ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን -የብልጽግና ፓርቲ ሊግ አባላት

50

ጊምቢ፣  ሚያዝያ 30 /2013/ (ኢዜአ) ምርጫው ሰላማዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የምዕራብ ወለጋ ዞን የወጣትና ሴት ሊግ አባላት አስታወቁ።

ህዝቡ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ወኪሉን እንዲመርጥ አባላቱ ጠይቀዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የምዕራብ ወለጋ ዞን ሴቶች ሊግ ሃላፊ ወይዘር ሜቲ ታፈሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ ምርጫ ፓርቲውን በመወከል የሚወዳደሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራትና ለክልል ምክር ቤት 11 ሴት እጩዎች ቀርበዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊና በህዝብ ዘንድ አመኔታን ያተረፈ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አባላቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

ህዝቡ ልማትን ያስቀጥላል፣ የሀገሪቱን ሰላም ያስከብራል ብሎ ያመነበትን  የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመውሰድ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጠይቀዋል ።

"ምርጫው ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ  ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻየን እወጣለሁ " ያለው ደግሞ የብልፅግና ፓርቲ የዞኑ ወጣቶች ሊግ አባል ጌታቸው ዋቅጋሪ ነው።

ወጣቱ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ይበጀኛል ያለውን ወኪሉን እንዲመርጥ ጠይቋል ።

"ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ወጣቱ የድርሻቸውን ለመወጣት ከወዲሁ መዘጋጀት አለበት" ሲል መልእክት አስተላልፏል።

"ድምጽ መስጠት ያለውን ዋጋ ስለምረዳ ከወዲሁ ለመምረጥ ካርድ ወስጃለሁ" ያለችው ደግሞ የሊጉ አባል ወጣት ኤልሳቤት ጂሬኛ ናት ።

"ለምርጫው ሰላማዊነትና ስኬታማነት የድርሻየን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ " ብላለች ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም