የህወሃትና ሸኔ በሽብርተኝነት መፈረጅ የንጹሐንን ሕይወት ከጥቃት ለመከላከል ያስችላል - የህግ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የህወሃትና ሸኔ በሽብርተኝነት መፈረጅ የንጹሐንን ሕይወት ከጥቃት ለመከላከል ያስችላል - የህግ ምሁራን
ባህርዳር፣ ሚያዚያ 30/2013 (ኢዜአ ) “ህወሃትና ሸኔ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ በጋራም ሆነ በተናጠል የሚፈጸም ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ ምሁራን ገለጹ።
በአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ምክር ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር አቶ ደሴ ስዩም ለኢዜአ እንደገለጹት ህወሃትና ሸኔ በአሸባሪነት የተፈረጁት በጸረ ሽብር ህጉ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማሟላታቸው በመረጋገጡ ነው።
“ሸኔም ሆነ ህውሃት ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ በመግደል፣ አካላቸውን በማጉደልና ንብረታቸውን በማውደም የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ መሆናቸውን የኢፌዴሪ ተወካዮች ምክር ቤት በማረጋገጡ ነው” ብለዋል።
በተለይም በህጻናትና ሴቶች ላይ የሰው ልጅ ይፈጽመዋል ተብሎ ከሚገመተው በላይ አሰቃቂ ድርጊቶችን በተከታታይነት በመፈጸማቸው በአሸባሪነት ለመፈረጅ እንዳበቃቸው አስረድተዋል።
“አንድ አካል ወይም ድርጅት በአሸባሪነት መፈረጁም ድጋፍና ትብብር የሚያደርጉለት ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግስታት እጃቸውን እንዲሰበስቡ በማድረግ አቅማቸውን ለማዳከምና ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ነው”ብለዋል።
“የጥፋት ቡድኖቹ በሽብርተኝነት መፈረጃቸውም ህብረተሰቡን በጋራም ሆነ በተናጠል ከሚፈጸምበት ጥቃት ለመከላከል ነው” ያሉት አቶ ደሴ “በህይወቱ፣ በአካሉና በንብረቱ ላይ በነዚህ አሸባሪ ቡድኖች ከፍተኛ በደል ሲደርስበት ቆይቷል” ብለዋል።
በዚህም ህብረተሰቡ ዛሬ የሚያየውንና የሚሰማውን ለሚመለከተው የጸጥታ አካል በማሳወቅ ራሱንና አካባቢውን ከጥፋት ከመታደግ ባሻገር ለወጣው ህግ ተገዥነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት አሳስበዋል።
አሸባሪዎቹ በጫካም ሆነ በሌላ አካባቢ ሆነው የጥፋት እቅዳቸውን የሚያወጡት፣ የሚዘጋጁትና የሚፈጽሙት ድርጊት ከህብረተሰቡ አይን የተሰወረ አይደለም ብለዋል።
ስለዚህ ህብረተሰቡ በራሱም ሆነ በሌሎች ወገኖች ላይ ጥቃቶችና የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ራሱን ፖሊስ በማድረግ በቁርጠኝነት መከላከል መቻል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
“በሁሉም አካባቢ መከላከያ፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አሰማርቶ የህዝቡን ደህንነት መጠበቅ አዳጋች በመሆኑ ህብረተሰቡ ሽብርተኞችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት” ብለዋል።
በክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍትሃ ብሄር ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው መስፍን በበኩላቸው እንደተናገሩት የመንግስት የመጀመሪያውና ዋነኛ ተግባሩ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ነው።
ይሁን እንጂ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል በቅራኔ ውስጥ የነበሩ ድርጅቶች በሰላማዊ መንገድ በሃሳባቸው መወዳደር የሚችሉበት እድል ለመፍጠር የተደረገው ጥረት በርካታ ችግሮችን ማስከተሉን ገልጸዋል።
በተለይም ህወሃትና ሸኔ ጥቃቅን ጥፋት ከመፈጸም አልፈው የጅምላ ጭፍጨፋና ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።
የጥፋት ቡድኖቹን በፈጸሙት ድርጊት ተመስርቶ ማስረጃ በማሰባሰብ በሽብርተኝነት መፈረጅ መቻሉ የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ መታየት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡም በአሸባሪነት የተፈረጁት ቡድኖች ስብስባቸውን፣ ዓላማቸውንና ግባቸውን በመመርመር አውቀውም ሆነ ሳያውቁ የነበራቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም አስረድተዋል።
“የሽብር ቡድን ነው ማለት ወንጀል ፈጻሚ ቡድን ነው” ያሉት አቶ ግዛቸው የነዚህ ቡድኖች አባልና ተባባሪ ሆኖ መገኘት በህግ የሚያስቀጣ መሆኑን ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ራሱን ማራቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ የማውጣት ስልጣኑን ተጠቅሞ ህወሃትና ሸኔ ሚያዚያ 28/2013 ዓ.ም በሽብርተኛነት መፈረጁ የሚታወስ ነው።