ቤተክርስቲያኗ ለዓመታት የነበረውን የመለያየት ግንብ አፍርሳ የፍቅር ድልድይ መገንባቷን በተግባር አረጋግጣለች-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

67
አዲስ አበባ  ሀምሌ 25//2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላለፉት 26 ዓመታት የነበረውን የመለያየት ግንብ አፍርሳ የፍቅር ድልድይ በመገንባት በተግባር ማረጋገጧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  በአሜሪካ የነበራቸውን ጉብኝትና የእርቅ ስነ-ስርዓት በተሳካ መልኩ አጠናቀው ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ጋር አብረው ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሆነው በሰጡት መግለጫ ፓትርያርክ ብፁዕ ወ ቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ አዲስ አበባ ቦሌ  ሲደርሱ ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ መልኩ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክስቲያን ለዓመታት የነበረባትን ግድግዳ  ሙሉ በሙሉ አፍርሳ አንድ መሆኗን ዛሬ በተግባር አረጋግጣለች። ይህም ለሙስሊሙ፣ ለካቶሊኩ፣ ለዋቄፈታዎችና የተለያዩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የቤተክርስቲያን አንድነት የሁሉም ደስታና ህብር ነውም ብለዋል። በሌላ በኩል ኤርትራም  ቤተክርስቲኗ  ለሁለት መከፈሏን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤  እነሱንም እንደዚሁ አንድ ማድረግና ማስታረቅ እንደሚገባና ለዚህም በቀጣዩ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። ዶክተር አብይ በአሜሪካ ቆይታቸው የተሳካ እንደነበርና የኃይማኖት አባቶች የእርቅ ሥነ-ሥርዓትም ሁሉን ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል። በእርቅ ሥር-ዓቱ ለተገኙት የሰሜን አሜሪካና የካናዳ ማህበረሰብ አባላትም ላደረጉት ተሳትፎ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ፓትርያርኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የቤተክርስቲያኗ አባቶች፣ ሊቃውንቶች፣ ካህናትና ምዕመናን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም