የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ የማስ ስፖርትና የምርጫ ቅስቀሳ መርሐ ግብር ተካሄደ

190

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 30/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ የማስ ስፖርትና የምርጫ ቅስቀሳ መርሐ ግብር ተካሂዷል፤ የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ነዋሪዎች ለብልጽግና ፓርቲ ላሳዩት ድጋፍም አመስግነዋል።

የስፖርት እንቅስቃሴ እና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብሩ “ህብረ ብሄራዊ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በመስቀል አደባባይ የተከናወነው።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ብልፅግና የእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት እንዲቀየር፣ ለውጡ እውን እንዲሆንና የኢትዮጵያውያን አንድነት እንዲጠናከር ይሰራል ብለዋል።

በመስቀል አደባባይ በሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለብልጽግና ያላቸውን ድጋፍ እና ፍቅር በማሳየታቸውም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ከህዝባችን ጋር በጋራ ሆነን ለሀገራችን ብልፅግና እንተጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በምክትል ከንቲባ ማእረግ የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ብልፅግና የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠንና ለሁሉም ምቹ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የብልፅግና አላማ ኢትዮጵያን በልማትና በብልጽግና ማስቀጠል አዲስ አበባን ውብና ምርጥ የአፍሪካ መዲና አድርጎ ማስቀጠል ነው ብለዋል።

በዝግጅቱ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 11ዱም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ በሽዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው ደጋፊዎች ማለዳ ላይ በመስቀል አደባባይ በመገኘት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርገዋል::

የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለስ አለምን ጨምሮ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም