የአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ያሻሽላል የተባለው የልማት ፖሊሲ ይፋ ሆነ

168

ሚያዚያ 30 ቀን 2013 (ኢዜአ)  የአርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ያሻሽላል የተባለው የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲና ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ።

ፖሊሲውና ስትራቴጂው በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀ ሲሆን በዛሬው እለት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ሆኗል።

ፖሊሲውና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂው ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኝ የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋቱም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ እስካሁን ራሱን የቻለ ፖሊሲ ባለመኖሩ አርብቶ አደሩን ፍትሃዊ የልማትና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ነፍጎት መቆየቱ ተገልጿል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን እንዳሉት የአርብቶ አደር ልማት ፖሊሲውና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂው አራት መሰረታዊ ጉዳዮችን የያዘ ነው።

ከእነዚህም ወስጥ የአርብቶ አደሩን የገቢ ምንጭ ማሳደግና የኑሮ ደረጃውን ማሻሻል፣ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን መሰረተ ልማቶች ማስፋፋት ይጠቀሳሉ።

የአርብቶ አደሩን የማስፈጸም አቅም መገንባትና መልካም አስተዳደርን ማስፈንም ሌላው ጉዳይ ነው ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ  በርካታ ፖሊሲዎች ቢወጡም ተግባራዊነታቸው ላይ ክፍተቶች መኖራቸው በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

ፖሊሲው ከወረቀት ባለፈ ተጨባጭ ውጤት እንዲያስገኝ በየደረጃው ያሉ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው በመግለጽ።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ስዩም መስፍንና የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ፤ የሚወጡ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሳይሆኑ ሲቀሩ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት በግልጽ የሚቀመጡበት አሰራር መኖሩን ነው የገለጹት።

በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ለፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነት በቁርጠኝነት በመስራት ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

የአርብቶ አደር ፖሊሲውም የታለመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ለዚህ ተብሎ ከተቋቋመው የልዩ ድጋፍ ኮሚቴ ጀምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሃላፊነት አለበት ብለዋል።

በአርብቶ አደሩ ፖሊሲ ይህን ክፍተት ለመሙላትና እያንዳንዱን ባለድርሻ ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።

ዶክተር ስዩም መስፍን በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት  በዋናነት ተጠያቂነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማድረግ የፖሊሲው ተግባራዊነትን ይረጋገጣል ብለዋል።

"የሰላም ሚኒስቴር ይሄንን የማስተባበር ሰፊ የሆነ ሃላፊነት አለበት ይሄም የማስተባበር ዋና ስራው ስራው እንዲሰራ ከማድረግ ባለፈ ስራ ያልሰሩ አካላት ካሉ ደግሞ እነኚህን ተጠያቂ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አልማዝ መሰለ ''ፖሊሲው ይፋ ስለሆነ ለአርብቶ አደሩ የተለየ ነገር አይፈጥርለትም መሬት ሊነካ ይገባል ስለዚህ ሁላችንም አተገባበሩ ላይ ሚና አለን ይሄንን ሚናችንን በተገቢው ከተወጣን የአርብቶ አደሩን ህይወት ይቀይራል" ብለዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ከኢትዮጵያ ህዝብ 12 በመቶ ያህሉ በአርብቶ አደርነት ይተዳደራል።

ከ60 በመቶ በላይ የአገሪቷን የቆዳ ሽፋን የሚሸፍነውም አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም