በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት ያላቸውን የምርጫ ታዛቢዎች አንቀበልም- የጋራ ምክር ቤት

89

ሚያዚያ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎትና አዝማሚያ ያላቸውን የምርጫ ታዛቢዎች እንደማይቀበል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ምርጫውን የመታዘብ ፍላጎት ያላቸው አገር አቀፍና አለምአቀፍ ታዛቢዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ህገ-መንግስት ሊያከብሩ እንደሚገባም አመልክቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ምክክርና የደረሰባቸውን የውሳኔ ሀሳቦች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው እንደተነሳው የአውሮፓ ህብረት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ ያለውን አፈጻጸም ታዝበው ምስክርነት እንዲሰጡ የጋራ ምክር ቤቱ ፍላጎት ነው።

ይሁንና ህብረቱ ምርጫውን መታዘብ የሚችለው የአገሪቷን ሉዓላዊነትና ህግ-መንግስቱን ባከበረ መልኩ ሊሆን ይገባል ብሏል።

የጋራ ምክር ቤቱ የፓርቲዎች ጉዳይና ስልጠና አስተባባሪ አቶ አላምረው ይርዳው እንዳሉት ህብረቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎቱን ምክር ቤቱ አይቀበለውም።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም በኢትዮጽያዊነታቸው የማይደራደሩና የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በቁርኝነት የሚሰሩ ናቸው ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በማይገባ መልኩ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ ምርጫውን እንዲታዘብ ያላቸውን ፍላጎትም ገልጸዋል።

ህብረቱ ቀደም ባሉት ዓመታት የተደረጉ የይስሙላ ምርጫዎችን ሲታዘብ መቆየቱን አስታውሰው አገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ እያደረገች ያለውን ጥረት ላለመታዘብ የወሰነበት ምክንያት አግባብ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።

ምርጫውን የመታዘብ ፍላጎት ያላቸው አገር አቀፍና አለምአቀፍ ታዛቢዎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ህገ-መንግስት ሊያከብሩ ይገባልም ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ  ህብረቱ ምርጫ ሲታዘብ መጠቀም በሚፈልገው የመረጃ ቴክኖሎጂ እና የምርጫ ውጤት ከምርጫ ቦርድ ቀድሞ ይፋ ላድርግ የሚሉት ፋላጎቶቹ “የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ስለሚፈታተን” ተቀባይነት እንደሌለው መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም