በትግራይ ክልል በሁለተኛው ዙር ድጋፍ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ መቻሉ ተገለፀ

57

ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) በትግራይ ክልል በሁለተኛው ዙር ድጋፍ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የሰላም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት  እንዳሉት  እስካሁን በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፉን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት ከአጋር አካላት ጋር  ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ለ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

በአንደኛና በሁለተኛ ዙር ድጋፍ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገም ገልጸዋል።

እስካሁን መንግስት ከክልሉ የቆዳ ስፋት 70 በመቶ ለሚሆነው ድጋፍ ሲያቀርብ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይ ግን ከክልሉ የቆዳ ስፋት 86 በመቶ የሚሆነው በውጪ  ድጋፍ  ሰጪዎች እንዲሸፈን እንደሚደረግ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

በቀጣይ በሚደረገው የድጋፍ አቅርቦት ላይ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ኬር፣  ወርልድቪዥን እና ፋሚሊሄልዝን ጨምሮ ስድስት ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳታፊ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በክልሉ 1 ሚሊየን የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ መጪው ክረምት በመሆኑ አርሶ አደሮች የግብርና  ስራዎቻቸውን  ማከናወን እንዲችሉ ከ126 ሺህ ኩንታል  በላይ ማዳበሪያና  ምርጥ ዘር  እንደሚቀርብላቸው ገልጸዋል፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ሰራተኛ ዶክተር አብዲ ዘነበ በክልሉ ከሚከናወነው የሰላም ማስከበር ስራ ጎን ለጎን የተቋም ግንባታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሁለት ሺህ የሚሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በሶስት ዙር ስልጠና እንዲያገኙና ደመወዝ እንዲከፈላቸው ተደርጓልም ተብሏል፡፡

እንዲሁም 400 ለሚሆኑ የክልሉ የፖሊስ አባላት በሶስት ዙር  ስልጠና  በመስጠት  በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

1 ሺ 300 በጎ ፈቃደኞችም ስልጠና ወስደው ማህበረሰቡን እንዲያግዙ ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም