ኮርፖሬሽኑ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ 7 ሚሊዮን በሚጠጋ ብር ቦንድ ገዛ

79

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ6 ሚሊዮን 927 ሺህ 200 ብር ቦንድ ገዛ።

ኮርፖሬሽኑ የቦንድ ግዥውን የፈጸመው "በእኛም ድጋፍ የግድባችን የስኬት ጉዞ ይቀጥላል" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የኮርፕሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የግድቡ ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱና የተፈጠረው የህዝብ መነሳሳት የኮርፕሬሽኑን አመራርና ሠራተኞች እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

ዓባይ አገሩንና ህዝቡን ለመካስ በተዘጋጀበት ታሪካዊ ወቅት በሕዳሴ ግድበ ግንባታ ሁሉም የአቅሙንና የሚችለውን እንዲወጣም አቶ ክፍሌ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ከ6 ሚሊዮን 927 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም አገርና ህዝብ በሚጠቅሙ የልማት ሥራዎች ኮርፖሬሽኑ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን አጋርነቱን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

በመገባደድ ላይ ያለውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስ ድጋፉ መጠናከርና ህዝቡም ተጠቃሚነቱን ማረጋጋጥ ይኖርበታል ብለዋል።

የግድቡ መጠናቀቅ ግብርናና ተያያዥ ሥራዎችን በማስፋትና በማዘመን አገርና ዜጎችን በኢኮኖሚ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ሃይሉ አብርሃም ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም