ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ከኬኒያ ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ

94

ድሬዳዋ ፤ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቁ።

በኬኒያ የሚኖሩ ኢትጵያዊያን ስደተኞች ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራ ቢጀመርም በኮሮና   ወረርሽኝ ሣቢያ መቋረጡ ይታወሳል፡፡

አሁን ላይ የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮልን በማሟላት በፈቀዳቸው ወደ ሀገራቸው መመለስ የጀመሩት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በድሬዳዋ አለም አቀፍ  አውሮፕላን  ማረፊያ   በመገኘት   የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር  አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ  አቀባበል  አድርገውላቸዋል።

አቶ ተስፋውን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ደህነታቸው ተጠብቆ በፍላጎታቸው ወደ  ሀገራቸው  የሚመለሱ  ኢትዮጵያዊያን 1ሺህ 688 ናቸው፡፡

ትናንት በመጀመሪያ ዙር የተመለሱት 66 ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ ጠቅሰው  የተቀሩት  ከነገ ጀምሮ እስከ ግንቦት መጨረሻ ተጠናቀው ወደ ሃገራቸው ይገባሉ ብለዋል፡፡

ተመላሾቹ ዛሬ ወደ ሱማሌ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ጋር  እንደሚቀላቁ  አመልክተው  ከክልሉ መስተዳደርና ከየዞኑ አስተዳደሮች   ጋር  በመሆን  አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው  አስታውቀዋል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን በበኩላቸው፤ ኢትጵያዊያን  ስደተኞች በፍላጎታቸው እንዲመለሱ መንግስት ያደረገውን ጥረትና ትጋት እንዲሳካ  ድጋፍ ላደረጉ የኬኒያ መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ  ኮሚሽንና  የአለም ምግብ ፕሮግራምን ምስጋና አቅርበዋል።

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች  ጉዳይ  ከፍተኛ  ኮሚሽን /ዩ ኤን ኤች ሲ አር/ የኢትዮጵያ  ተወካይ  ተመላሾቹ ዘላቂ ህይወታቸውን  እስኪመሰርቱ ከመንግስት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ  አስታውቀዋል፡፡

ዩ ኤን ኤች ሲ አር ለተመላሾቹ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን  የሚያሟሉበት መነሻ ገንዘብም ሰጥቷል ብለዋል፡፡

ከተመላሽ ኢትዮጵያዊያን መካከል ወይዘሮ ሞሚና መሐመድ ለ11 ዓመታት  ኬኒያ  በስደት እንደኖሩና የስድስት ልጆች እናት እንደሆኑ በመጥቀስ ለተደረገላቸው  አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

"አሁን ወደተወለድኩበት ደገሃር እመለሳለሁ፤ ሀገርን  የመሰለ ታላቅ ፍቅርና ደስታ የለም" ያሉት ወይዘሮ ሞሚና ከልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታና በነጻነት ለመኖር  መዘጋጀታቸውን  ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ በሱማሌ ክልል በነበረው ጨቋኝ አስተዳደር ከሀገራቸው ወጥተው 12 ዓመታት  ኬኒያ ኖረው እንደተመለሱ የገለጹት ደግሞ  ሌላው  ተመላሽ  ኢትዮጵያዊ  አቶ አብዱልመጂድ መሐመድ ናቸው።

ከሌሎች ጋር በመተባበር ሰርተው ለመኖር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ በተለያዩ ሃገራት ጥገኝነት ጠይቀው ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው  በመመለስ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም