የአውሮፓ ህብረት ከምርጫ ታዛቢነት መውጣቱ በምርጫው ሂደት የሚያመጣው ለውጥ የለም ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ

62

ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ታዛቢነት መውጣቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

የአውሮፓ ህብረት ሊልከው የነበረውን የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሰረዙን ተከትሎ  መንግስት  በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ መስጠቱ ይታወሳል።

ህብረቱ የምርጫውን ውጤት ምርጫ ቦርድ ይፋ ከማድረጉ በፊት ልግለጽ የሚል እና ያልተፈቀደ የቴክኖሎጂ መሳሪያ ይዤ መግባት አለብኝ በሚል የኢትዮጵያን ነጻነት ሊጋፉ የሚችሉ ጉዳዮች በማንሳቱ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ሃላፊዎች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአውሮፓ ህብረት  ምርጫ ታዛቢ ቡድን በምርጫው አልሳተፍም ማለቱን በተመለከተ ፓርቲያቸው ያለውን  እይታ ገልጸዋል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌትነት ወርቁ የህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ቀደም ሲል  በተካሄዱ ምርጫዎች የነበረውን ተሳትፎ በማስታወስ የአሁኑ ውሳኔ የተለየ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ከገደባቸው አልፈው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ለማገዝ  ሲሞክሩ እንደነበር አውስተው በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሳማኝነት ላይ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።

ዋና ጸሃፊው የኢትዮጵያ መንግስት ከሲቪል ማህበራት፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአገር  ሽማግሌዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከኢትዮጰያዊያን ጋር ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ  ለማድረግ የበለጠ መስራት እንደሚጠይቀው አመላክተዋል።

በመሆኑም የምርጫው ተአማኒነት የሚረጋገጠው በውጭ ታዛቢዎች ብቻ ሳይሆን  በኢትዮጵያዊያን ትብብር  መሆኑን ገልጸዋል።

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው ይርዳው በበኩላቸው  የአውሮፓ  ህብረት ከምርጫ ታዛቢነት መውጣቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ላይ የሚያመጣው  ለውጥ አለመኖሩን አስረድተዋል።

ህብረቱ የአገርን ክብር በማይነካ መልኩ አለም አቀፍ መርህን ተከትሎ መታዘብ ቢችል መልካም መሆኑን አንስተው፤ ምርጫውን ተአማኒ የማድረግና ያለማድረግ ጉዳይ  የኢትዮጵያዊያን እንጂ የታዛቢዎች አለመሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ  ከበደም እንዲሁ ህብረቱ ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ የአንድን አገር ሉአላዊነት  የሚጋፋ  መሆኑን ነው የተናገሩት። 

እንደ አንድ ሉአላዊ አገር የውጭ ታዛቢ ባይኖርም የምርጫውን ሂደት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል።  

ፓርቲያቸው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የጸጥታ ችግር ቢኖርም በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት መጨረሻና ሰኔ መጀመሪያ በምታካሂደው ጠቅላላ ምርጫ  የሚሳተፉ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ ሃሳብ በመገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ዘዴዎች  ለመራጩ ህዝብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም