መጪው ምርጫ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጣ የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለጸ

74

አዳማ፤ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ) በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የድርሻውን እንደሚወጣ የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ በምርጫ ታዛቢነት ዙሪያ  ከኦሮሚያ 20 ዞኖችና ሁሉም የከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ  ሴት አመራሮች በአዳማ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል ።

ዛሬ በተጀመረው የስልጠና መድረክ የተገኙት የኦሮሚያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አስካለ ለማ እንዳሉት፤ ፌዴሬሽኑ ስድስተኛ ጠቅላላ  ምርጫ ለመታዘብ ከምርጫ ቦርድ ፍቃድ አግኝቷል።

ምርጫው በህዝቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያተረፈና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን በታዛቢነት ሚናችንን ለመወጣት ዝግጅት እያጠናቀቅን ነው ብለዋል ።

በተለይም ህዝቡ ህገ መንግስታዊ መብቱን ተጠቅሞ በወሰደው ካርድ ለሚፈልገው ፓርቲ ድምፅ እንዲሰጥ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ሂደቱን እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኘሮግራማቸውን የማስተዋወቅ ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን፣ የድምፅ አሰጣጡም ግልፅነት የተሞላበትና የህዝብ ድምፅ እንዲከበር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን በሰለጠነ መንገድ የሚፈቱበትን  አቅም ለመፍጠር ጭምር ስልጠናው የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ወይዘሮ አስከለ አስረድተዋል።

በምርጫው ሂደት የመራጩ ህዝብ ጤንነት እንዲጠበቅ ኮሮናን ለመከላከል የወጣው ፕሮቶኮል መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲሆን ትምህርታዊ ግንዛቤ እስከ ቀበሌ ድረስ እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

በክልሉ ለመራጭነተ  ይመዘገባል ተብሎ ከሚጠበቀው ህዝብ ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ እንዲወስዱ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የሚጠበቀው ማሳካት የሚያስችለን ደረጃ ላይ ነን ብለዋል።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ ፕሮግራሞቻቸውን ለህዝቡ በማቅረብ በሃሳብ የተሻሉ ሆነው መገኘት እንደሚጠበቅባቸውን አመልክተዋል።

ፓርቲዎች ይህንን ተገንዝበው ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ማህበሩ ለመታዘብ ያገኘውን ዕድል በአግባቡ ተጠቅሞ የህዝብን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ሽታዬ ደሳለኝ ናቸው።

ከመራጮች ምዝገባ ሂደት ጀምሮ በዞን፣ ከተሞች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ድረስ እየሰራን ነው ብለዋል ።

ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲደረግ ሴቶች ድምፃቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የድምፅ ብክነት እንዳይኖር የፓርቲዎች ምልክቶችን በትክክል አውቀው ለሚፈልጉት ድምጽ እንዲሰጡ ለማስቻል በሚካሄደው እንቅስቅሴ ውስጥ የድርሻቸው ለመወጣት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

የማህበሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሽቶ ሊኪሳ በበኩላቸው ፤ ምርጫው ሰላማዊ ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ገለልተኛና ነፃ እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል።

ስልጠናው  ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም