"ህወሃትና ሸኔ " በአሸባሪነት መሰየማቸው ተገቢ ነው ... አስተያየት ሰጪዎች

82

ሚያዝያ 28/2013(ኢዜአ)የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት "ህወሃትና ሸኔን "በአሸባሪነት የሰየመበት ውሳኔ ተገቢና ሌሎችን የሚያስተምር ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 6ኛ አመት የስራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ከሚኒስትሮች ምክር ቤት "ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት)" እና "ሸኔ" በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ማጽደቁ ይታወቃል።

ይህን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች "ህወሃትና ሸኔ" አሸባሪ ሊያስብላቸው የሚችል ተግባር ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ የሚያውቀውና በጥቅምት ወር ህወሃት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ የከተተ እንደነበር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አቶ መላኩ ተሰማ ገልጸዋል፡፡

በሽብር ጥቃቶች በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን እያጡ መሆኑንና ተግባሩ አገሪቱን ለማፍረስና ህልውናዋን አደጋ ውስጥ ለመክተት የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዚህ አይነት ወንጀሎችን በቸልታ ማለፍ መንግስት ህግ በማስከበር የላላ አቋም ያለው ስለሚያስመስለው ውሳኔው በአገር ወስጥና በውጭ ላሉ ጠላቶች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን አቶ መላኩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በአሸባሪ ቡድኖቹ ሴራ ብዙ ወገኖች ህይወታቸውን ያጡ በመሆኑንና ቡድኖቹም ይህንኑ ባለመካዳቸው እርምጃው ትክክል ነው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበበ ሲሳይ ናቸው፡፡

የተወሰደው እርምጃ ለሌሎችም ትምህርት የሚሰጥና ህዝቡም በመንግስት ውሳኔ ደስተኛ እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑንም አቶ አበበ ጠቅሰዋል፡፡

ሽብር ፈጻሚውን አካል ብናውቀውም እስከ አሁን በሽብርተኝነት አለመፈረጁ እንደ ዘገየ ፍርድ የሚቆጠር ነው በማለት ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቁምነገር ገዛኽኝ ውሳኔውን አስመልክተው ተናግረዋል፡፡

መንግስት ራሱን በማጥራትና ወደ ውስጥ በመመልከት ለውጡን ለማስቀጠል ካልተጋ ይቸገራል ብለው እንደሚያስቡም አቶ ቁምነገር ይናገራሉ።

ወጣት ቴዎድሮስ በላይ በበኩሉ ውሳኔው መዘግየቱንና ቀደም ብሎ ቢወሰን ኖሮ ብዙ ጥፋቶቸን ማስቀረት ይቻል ነበር ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ መንግስት ውስጥ ተሰገስገው ሌላ ስራ የሚሰሩ አካላት በመኖራቸው ራሱን ማጥራት አለበት በማለትም ነው የገለጸው።

በውሳኔው ላይ አስተያየት አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች የመንግስት ውሳኔ የዘገየ ከመሆኑ በስተቀር ተገቢ መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም