በጌዴኦ ዞን ከ18 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ለተከላ ተዘጋጀ

198

ዲላ ፤ሚያዝያ 28/2013 (ኢዜአ ) በጌዴኦ ዞን በተያዘው ዓመት ለተከላ የሚበቃ ከ18 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መዘጋጀቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገለጹ።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከመምሪያው ጋር በመተባባር ለአካባቢው የቡና ልማት ድጋፍ እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

በመምሪያው የቡና ልማት ባለሙያ አቶ ምርታገኝው በቀለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ችግኙ የተዘጋጀው በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት በታቀደው መሰረት የሚከናወን ነው።

ከዚህ በፊት ይተከል የነበረው  የቡና ችግኝ ምርት ለመስጠት ሶስት ዓመት  እንደሚፈጅበትና አሁን ለተከላ የተዘጋጀው ዝርያ  ተገቢው እንክብካቤ ከተደረገለት በአንድ ዓመት ውስጥ ምርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ችግኙ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በመንግስት የችግኝ ጣቢያዎችና በአርሶ  አደር ማሳ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ያረጁ ቡናዎች ነቀላ ፣የጉድጓድ ቁፋሮና የአፈር ማልበስ ስራ እንዲሁም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላጠናቀቁ አርሶ አደሮች ከተዘጋጀው ችግኝ በማሰራጨት እየተተከለ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለተከላ የሚሆን ጉድጓድና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ላዘጋጁ አርሶ አደሮች 300 ሺህ ችግኞችን ማከፋፈላቸውንም ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ከቡና ምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ዝርያዎችን በምርምር ከማሻሻል ባለፈ በምርት አሰባሰብና የገበያ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው የቡና ምርምር ማዕከል ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዞኑ ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋ ቀበሌ አርሶ አደር ወርቅዬ ሻሎ በሰጡት አስተያየት፤ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ሄክታር ማሳቸው የተከሉት የተሻሻለ ዝሪያ ያለው ቡና በዓመቱ ምርት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

በተያዘውም ዓመት ቀደም ብለው ያረጀ ቡናን አስወግደው ከ1 ሺህ በላይ የተሻሻለ የቡና ዝርያ ለመትከል ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ከመንግስት ባገኙት የተሻሻለ የቡና ዘር ከ12 ሺህ በላይ ችግኝ ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር የሹ ሻሎ ናቸው።

የተሻሻለው ዝርያ በሽታን የሚቋቋምና በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ በሌላውም አርሶ አደር ዘንድ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ካዘጋጁት ችግኝ ለራሳቸው አስቀርተው ቀሪውን በመሸጥ እየተጠቀሙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም