የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ግዛት በሃይል ለመያዝ ቢፎክርም እንደማይሳካለት የአሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ

108

አሶሳ፤ሚያዚያ 28/2013(ኢዜአ) የሱዳን መንግስት "የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት የእኔ ነው" በማለት የኢትዮጵያን ግዛት በሃይል ለመያዝ የሚያሰማው ፉከራ ከምኞት ባለፈ እንደማይሳካለት በአሶሳ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝብ የሃገር ውስጥ ችግሮችን መፍታት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፈቃዱ ወልደመስቀል እንዳሉት፤ ሱዳን አሁን እንደሃገር እንድትቀጥል ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከፍተኛ እገዛ አድርጋለች፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሃገሪቱ የተሰከሰተውን አለመግባባት በውይይት እንዲፈታ በማድረጋቸውን ወደ መረጋጋት እንድትመጣ ያደረጉትን አስተዋጽኦ ነዋሪው ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ለሱዳን መጠናከር የከፈሉትን መስዋዕትነት የሀገሪቱ መንግስት ዘንግቷል ብለዋል፡፡

የሱዳን መንግስት ከሰሞኑ “የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት የእኔ ነው” በሚል የሠጠው መግለጫ የሚመካው ጉዳይ እንዳለ ያሳያል ያሉት አቶ ፈቃዱ ፤ይህም በተለይ ኢትዮጵያ እንድትበታተን የሚፈልጉ በገንዘብ የተገዙ የሃገር ውስጥ የጥፋት ሃይሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሱዳን መንግስት መግለጫ ከፉከራ አያልፍም ያሉት ነዋሪው፤ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ህዝብ እና መገናኛ ብዙሃን ከውጭ ጠላት ይልቅ የውስጥ ችግሮቻቸው ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵውያን መገለጫቸው ተስፋፊነት ሳይሆን አብሮ ማደግ እንደሆነ ጠቁመው፤ ለዚህም ዘረኝትን በመተው አንድነታቸውን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል፡፡

ሀገሪቱ አሁን የገጠማትን ፈተና ከህዳሴው ግድብ ጋር ቀጥታ ተያያዥነት እንዳለው የገለጹት ነዋሪው፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ችግሩ አብሮ ይቋጫል በማለት፤ ሃገሪቱ በአካባቢውም ሆነ በዓለም ያላት ተቀባይት ከፍ እንደሚል አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጠላት ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ ድንበር አልፎ ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት አድርጓል ያሉት ደግሞ አቶ አብዱልሻፊ ሼህ ኢብራሂም ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ግዛት በሃይል ለመያዝ የሚደረግ የሱዳን መንግስትም ሆነ የሌላ የውጪ ሃይል ምኞት መቼም ቢሆን እንደማይሳካ ገልጸዋል፡፡

ጠላት የህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ ከውስጥም ሆነ ከውጪ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ "በተባበረ ሃይላችን አሸንፈን ፕሮጀክቱን ለፍጻሜ እንደምናበቃ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል፡፡

አቶ ኡመር አብደላ በበኩላቸው፤ የሱዳን መንግስት አዲስ አበባንም የእኔ ነው ብሎ መግለጫ ማውጣት ቢችልም አሳልፎ የሚሰጣቸው ማንም ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱ የሱዳን መንግስት የሃገር ውስጥ አሸባሪዎችን ይዞ ሃገር ለማፍረስ የሚደያርገው ጥረት ነው ያሉት ነዋሪው ፤ኢትዮጵያዊያን አንድነታቸውን በማጠናከር የውጪ ጠላቶች መመከት አለባቸው ብለዋል፡፡

ሌላው ነዋሪ ሼህ አለሃሰን ኢብራሂም በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያን ለማዳከም የተነሱ የውጪ ሃይሎች እንቅስቃሴ እንደማያሳጋቸው ገልጸው፤ይልቁንም የሚያሰጋን የውስጥ ችግራችን ነው፤ መንግስት ትኩረት መስጠት ያለበት ጉዳይ ይኸው ነው ብለዋል፡፡

የህዳሴው ግድብም ሆነ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢትዮጵያ ውስጥ እስከሆኑ ድረስ የክልሉ መሬትም ሆነ የግድቡ ባለቤትነት የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑ ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም