በኢትዮጵያና ኖርዌይ መካከል ያለው የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር ገለጹ

108
አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2010 በኢትዮጵያና ኖርዌይ መካከል ያለው የአየር ንብረት ለውጥ የትምህርትና የዲሞክራሲ ግንባታ የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር ገለጹ። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስራ ቆይታቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሬስ ጋርደርን ዛሬ አሰናብተዋል። አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያና ኖርዌይ በትምህርትና ጤና፣ በኃይል፣ በአየር ንብረት ለውጥና ዲሞክራሲ ግንባታ በቅንጅት እየሰሩ ነው። በቆይታቸውም የሁለቱ አገሮች ሁለንትናዊ ትብብር እንዲጠናከር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት ሲሰሩ እንደነበርና ወደፊትም የሁለቱ አገራት የልማት ትብብር ተጠናከሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ኖርዌይ ቀጥታ በረራ መጀመሩ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የኖርዌይ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራታቸው፣ በማዕድንና በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትና ሌሎች ዘርፎች በቅንጅት በመስራት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንዲጠናከር ተደርጓል ብለዋል። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው አምባሳደር አንድሬስ ጋርደር በቆይታቸው በሁለቱ አገሮች የልማት ትብብር እንዲኖር ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። ኢትዮጵያ ኖርዌይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የልማት ትብብር ተጠቃሚ አደርጋ ካቀፈቻቸው 12 አገራት ውስጥ አንዷ በመሆኗ የልማት ትብብሩ ተጠቃሚ እንድትሆን አምባሳደሩ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል ነው የተባለው። በዚህም ባለፈው የፈረንጆቹ 2017 የልማት አጋርነቷን ለማሳየት 61 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያደረገች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለምታካሄደው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ  ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን  ገልጸዋል። የኖርዌይ ያራ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ፖታሽዬም ከማምረትም ባለፈ በማዳበሪያ ምርት ላይ ለመሰማራት ስምምነት ላይ ሲደረስም የአምባሳደሩ ጥረት የጎላ እንደነበር አውስተዋል። ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ኖርዌይ የልማት አጋርነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አዲሱ አምባሳደርም አበክረው እንዲሰሩ መጠየቃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዘዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም