የኮቪድ -19 የስርጭትን ለመከላከል አዲስ መመሪያ ይፋ ሆነ

74

ሚያዚያ 26/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ የሚታየውን የኮቪድ -19 ስርጭት ለመከላከል የሚረዳና ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር አዲስ መመሪያ ይፋ አደረገ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካሉ መመሪያውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

አዲሱ መመሪያ በመዲናዋ እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መውጣቱን ጠቁመዋል፡፡

በወጣው መመሪያ መሰረት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅምና የመከላከያ ፕሮቶኮል ተቀምጦላቸዋል፡፡

በዚህም ሚኒባስ ታክሲ በወንበር ልክና ከኋላ ሶስት ሰዎችን እንዲጭኑ፤ ሃይገርና ቅጥቅጥ አውቶብሶች በወንበር ልክና አምስት ሰዎችን ራቅ ራቅ ብለው የሚቆሙ እንዲጭኑ መመሪው እንደሚያስገድድ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም አንበሳና ሸገር አውቶቡሶች ፣የመንግስት ሰራተኞች ሰርቪስና ድጋፍ ሰጭ አውቶቡሶች በወንበር ልክ እንዲጭኑና የሚቆሙ ሰዎችን ቁጥር ደግሞ ከዚህ በፊት ከሚጭኑት 50 በመቶ ቀንሰው መጫን እንዳለባቸው በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

ባጃጆች ሹፌሩን ጨምሮ ሶስት ሰዎች እንዲጭኑ፤ የቤት መኪኖች፣ ላዳ ታክሲዎችና አምስት ሰዎች የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች አራት ሰዎችን ብቻ መጫን እንዳለባቸው በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ጠዋት ስራ ከመጀመራቸው በፊትና ቀን ስምንት ሰዓት ላይ ተሽከርካሪዎቻቸውን ማጽዳት (ዲስኢፌክት ማድረግ) እንደሚገባቸውም ተገልጿል፡፡

አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ማስክ ያላደረጉ ተሳፋሪዎችን መጫን እንደሌለባቸውም መመሪያው ያዛል፡፡

መመሪያውን ተላልፈው ከልክ በላይ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች ላይ የተለያዩ ቅጣቶች ተቀምጠዋል፡፡

ሚኒባስ ታክሲዎች አንድ ሺህ ብር፤ አንበሳ፣ ሸገር፣ ሃይገርና ቅጥቅጥ አውቶቡሶች 1 ሺህ 500 ብር፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል፣ ላዳና ሜትር ታክሲዎች ደግሞ 500 ብር እንደሚቀጡ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

ታሪፍን በተመለከተ በአገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል ከተደረገው ማስተካከያ ውጪ አዲስ ጭማሪ አለመደረጉ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ከዚህ በፊት ከወጣው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍል ማንኛውም አሽከርካሪ 1 ሺህ 500 ብር ይቀጣል ተብሏል፡፡

አሽከሪካሪውና ረዳቱ ማስክ ካላደረጉ አንድ ሺህ ብር፣ ማስክ ያላደረግ ተሳፋሪ ከጫኑ በአንድ ሰው 500 ብር እንደሚቀጡ ተደንግጓል፡፡

ተሽከርካሪዎቻቸውን ዲስኢንፌክት ሳያደርጉ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች ደግሞ ሁለት ሺህ ብር መቀጮ እንደተጣለባቸው ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ከተመደበበት መስመር ውጪ የሚሄድ አሽከርካሪ በመደበኛው የታሪፍ ቅጣት እንደሚቀጣም ተገልጿል፡፡

ከባድ ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 10 እስከ 12 ሰዓት እንዳይንቀሳቀሱ ገደብ መጣሉ እንዳለ ሆኖ ከሰኞ እስከ አርብ የነበረው ገደብ ተሻሽሎ ቅዳሜን ጨምሮ የሚተገበር መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ይህንን ገደብ የሚተላፍ የከባድ መኪና አሽከርካሪ አምስት ሺህ ብር እንደሚቀጣ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

ገደቡ በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሰሩ ከባድ ተሽከርካሪዎችን እንደማያካትት ነው የተጠቆመው፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፤ የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲና የመዲናዋ ፖሊስ ከዛሬ ጀምሮ የመመሪያውን አፈጻጸም በጋራ የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ እንደሚጀምሩ ኢንጂነር ስጦታው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም