ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ጸጥታን በማስከበር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የፖሊስ አባላት ገለጹ

63

ጊምቢ፤ ሚያዝያ 26 /2013 (ኢዜአ) ስድስተኛው ጠቅለላ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጸጥታን በማስከበር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ በምዕራብ ወለጋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የፖሊስ አባላት ገለጹ፡፡

የፖሊስ አባላቱ እንዳሉት፤ ምርጫውን የሚያውክ ነገር በምንም ዓይነት መልኩ ተቀባይነት የለውም።

በምርጫው የሚወዳደሩ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል ለማገልገል አቅደው  ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል።

ለምርጫው ስኬታማነት ከየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ነፃና ገለልተኛ  በመሆን ህግንና  ፖሊሳዊ  ሥነምግባር በማክበር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ከዞኑ የፖሊስ አባላት መካከል ረዳት ኢንስፔክተር አበራ ጋቢሳ በሰጡት አስተያየት፤ መጪው ሀገራዊና  ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ጸጥታንና የህግ የበላይነት በማሰጠበቅ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከየትኛው ፓርቲ ነጻና ገለልተኛ በመሆን  ለምርጫው ሰላማዊነት  ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ  አመልክተዋል፡፡

በዞኑ የላሎ አሳቢ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፐክተር መርጋ ያደታ በበኩላቸው፤ በቅድመና ድህረ ምርጫው ላይ ያሉ ሂደቶች ዴሞክራሲያዊ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የመጀመሪያው ጉዳይም ምርጫውን ነፃ ማድረግ ነው ያሉት ሃላፊው፤ ለዚህም የወረዳው ፖሊስ በቁርጠኝነት ለመሰራት መዘጋጀቱን  ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ፖሊስ ሰላም ማስከበር መሰረታዊ የስራ ሂደት መሪ ሳጂን ብርሃኑ ምትኩ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች በተለይም ስልጣን ላይ በቆየው የፖለቲካ ፓርቲ ጫናና ግፊት ሲደረግባቸው ነበር።

የአሁኑ ምርጫ ግን በፊት ከነበሩት ከወዲሁ ካለው ዝግጅት ጀምሮ በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንዲሆን ህግንና ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር በመጠበቅ  ሃላፊነቱን እንደሚወጣ  ተናግረዋል።

ለዚህም የዞኑ የፖሊስ አደረጃጀት ከየትኛውም ፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በገለልተኝነት ለምርጫው ስኬታማነት የፀጥታ ማስከበሩን ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም