በኃይማኖት መሪዎች መካከል የተፈጠረው እርቀ ሰላም የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ትልቅ አቅም አለው- የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

136
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010በኃይማኖት መሪዎች መካከል የተፈጠረው እርቀ ሰላም የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንዳለው የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ቅራኔ ምክንያት ቤተክርስትያኒቷ አንድነቷን አጥታ እንደነበር ይታወቃል። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ ለኢዜአ እንደገለጹት የሲኖዶሱ ወደ አንድነት መምጣት "በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታትና ወደ አንድነት ለማምጣት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው"። የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የጉባኤው የበላይ ጠባቂ ሼህ መሐመድ አሚን ጀማልም የሲኖዶሶቹ ወደ አንድነት መምጣት ለአገሪቱ የሰላምና የልማት ስራዎች የሚኖረውን አስተዋጽኦ ተናግረዋል። በእምነቱ ተከታዮችና በአጠቃላይ የአገሪቷ ህዘቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከርና በብሄርና በሌሎች ልዩነቶች ሳቢያ መከፋፋልን ለማስወገድም እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና የእምነቱ አባቶች ልዩነቶችን በማስወገድ በአንድነት ሙስሊሙን ለማገልገል የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል። በቅርቡ በአዲስ መልክ በተቋቋመው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እና የእምነቱ አባቶች እና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት መካከል እየተደረገ ያለው ውይይትም በጋራ ለመስራት ወደ ሚያስችል ስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም መጋቢ ዘሪሁን ገልጸዋል። ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል እንደሚሉትም የሲኖዶሶቹ እርቅና ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ጋር እየተደረገ ያለው ውይይት ለጉባኤው የሰላምና የልማት ስራዎችን የጋራ ስራ ለማጠናከር እንዲሁም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው። በኦርቶዶክስ ተዋህዶና በሙስሊም ኃይማኖት መሪዎች መካከል እየተደረጉ ያሉ የዕርቅና የሰላም ስምምነቶችን ሌሎች የኃይማኖት ተቋማትም ሊተገብሯቸው የሚገቡ ተሞክሮዎች ናቸው ብለዋል። የኃይማኖት ተቋማት የይቅርታ፣ የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት መሆን እንጂ የግጭትና መከፋፈል መንስኤ መሆን የለባቸውም ሲሉም ተናግረዋል። ሁሉም ኃይማኖቶች የሚሰብኩት ፍቅርና አንድነትን በመሆኑ በኃይማኖቶች መካከል ቅራኔን በማስወገድና በጋራ በመሆን ጠንካራ ስራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል። በሌላ በኩል ወጣቶች የአገሪቱን ሰላምና አብሮነት ለማደፍረስ ለሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መፍቀድ እንደሌለባቸውም መክሯል ጉባዔው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም