የስፖርት መሰረታዊ መርሆው በስነምግባር መታነጽና ሰላማዊ መሆን ነው_የብስክሌት ስፖርተኞች

110
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 'ስፖርት ሰላም ነው ስፖርት ፍቅር ነው ስፖርት አንድነት ነው' ይላሉ የብስክሌት ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞች። የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ከግንቦት 6 እስከ 11 ቀን 2010 ዓ.ም አራት ኪሎ ስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል ለብስክሌት ተወዳዳሪዎች፣ አሰልጣኞችና ቡድን መሪዎች በስፖርታዊ ጨዋነት፣ ስለ ህክምና፣ የትራፊክ ደህንነትና የአሰልጣኝነት መርሆዎች ላይ የሚሰጠውን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ዛሬ ጀምሯል። የኢዜአ ሪፖርተር በስልጠናው መክፈቻ ላይ በመገኘት የብስክሌት ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞችን በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ አነጋግሯል። ላለፉት 10 ዓመታት በብስክሌት ስፖርት ውስጥ ያሳለፈው የኢትዮ ኤሌትሪክ ብስክሌት ቡድን ተወዳዳሪ አሰግድ ሃይሉ ከውጤታማነት ባለፈ ስፖርት መሰረታዊ መርሆው በስነምግባር መታነጽና ሰላማዊ መሆን እንደሆነ ይናገራል። በብስክሌት ስፖርት ውድድር ሆነ ልምምድ ስፖርተኛው ቢወድቅ የቡድን አጋሩም ሆነ ተፎካካሪው አንስቶና ድጋፍ አድርጎ ወደ ልምምዱና ወደ ውድድሩ እንዲመለስ የሚያደርግ እንደሆነ ገልጿል። 'ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ አሸናፊ ከተሸናፊ ተቃቅፎ ሰላምታ ይለዋወጣል ተወዳዳሪው በስፖርት ማሸነፍና መሸነፍን እንዳለ ስለሚያምን ያንን በጸጋ ተቀብሎ ይሄዳል እንጂ ጸብና ድብድብ በፍጹም አይታሰብም' ይላል የብስክሌት ተወዳዳሪው አሰግድ። በአንዳንድ ስፖርቶች በተለይም በእግር ኳስ ላይ እየታየ ያለው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ችግር አሳዛኝና የስፖርት መሰረታዊ መርሆዎችን የሳተ እንደሆነ ተናግሯል። የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ሳይባባስ በዘላቂነት እንዲፈታ በየትምህርት ቤቱ በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባና ስፖርተኛውን ከውጤታማነትና ብቃት ባለፈ በስፖርታዊ ስነምግባር ተኮትኩቶ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግሯል። የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነችው ፍሬህይወት ተሻለ በብስክሌት ስፖርት ውስጥ የጎላ የሚባል የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እንደሌለ ገልጻለች። በውድድሮች ላይ ብስክሌት ከብስክሌት ሲጋጩ ተወዳዳሪዎች ከሚያሳዩት መበሳጨትና ስሜታነዊነት አልፎ የስፖርታዊ ጨዋነት ግድፈት ጎልቶ እንደማይታይ ተናግራለች። በእግር ኳሱ ላይ የሚታዩ የስነምግባር ጉድለቶች ፍጹም ተቀባይነት እንደሌላቸውና የስፖርትን ሰላማዊ ገጽታ የሚያጠፉ እንደሆነ ጠቁማለች። ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ስደተኞች የተቋቋመው የአፍሪካ የብስክሌት ቡድን ተወዳዳሪ መሐሪ ሃይሌ፤  በብስክሌት ስፖርት ውድድር ላይ የወደቀን ተወዳዳሪ ማለፍ ፍጹም የማይደገፍ እንደሆነ ገልጿል። የወደቀውን ተወዳዳሪ በማንሳት ወደ ውድድሩ እንዲመለስ ማድረግ ትልቅ የስፖርታዊ ፍቅር ማሳያ እንደሆነ ተናግሯል። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የብስክሌት ክለብ አሰልጣኝ ሮቤል ገብረማርያም የስፖርታዊ ጨዋነት መርሆዎችን የሚጥሱ አካላት ላይ ጠንካራና አስተማሪ የሚባል እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ነው የሚገልጸው። የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳነት አቶ ረዘነ በየነ ስልጠናው አሁን በስፖርታዊ ጨዋነት እየታዩ ካሉ ጉድለቶች አንጻር ጊዜውን የጠበቀ እንደሆነ ተናግረዋል። በእግር ኳሱ ላይ እየታየ ያለው ችግር ወደ ሌሎች ስፖርቶችም እንዳይዛመትና ጥንቃቄ ለማድረግ ፌዴሬሽኑ ይህን ስልጠና ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም