በእንጅባራ ከተማ በ36 ሚሊዮን ብር የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት በቁ

67
ባህርዳር/ አክሱም ሃምሌ 25/2010 በእንጅባራ ከተማ በ36 ሚሊዮን ብር ግንባታቸው የተጠናቀቁ የመሰረተ ልማት አውታሮች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የአስተዳደሩ ከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት አስታወቀ ። በሌላ በኩል በአክሱም ከተማ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አዲስ የአስፋልት መንገድ ለመገንባት ስምምነት ተደርጓል። በእንጅባራ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተገንብተው ለአገልግሎት ከበቁ የመሰረተ ልማት አውታሮች መካከል 16 ሜትር ስፋት ያላቸው ሦስት ድልድዮችና 18 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ እንደሚገኙበት በጽህፈት ቤቱ የቤቶችና መሰረተ ልማት ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ጌታቸው ይመኑ አስታውቀዋል ። በተጨማሪም የ27 ኪሎ ሜትር የውሃ ማፋሰሻ ቦይ፣ የመጠጥ ውሃና ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውንም አመልክተዋል። "በመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ ለ1 ሺህ 200 ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል " ያሉት ቡድን መሪው መሰረተ ልማቶች የህዝቡን ፍላጎትና የከተማዋን እድገት መሰረት በማድረግ የተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወይዘሮ ትግስት አላምረው በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው የተሰራው የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ከበጋ አቧራና ከክረምት ጭቃ እንደታደጋቸው ገልጸዋል። ለመንገዱ የተሰራለት የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይም በመደበኛነት ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለአካባቢው ውበት መሆኑን ተናግረዋል። በተያያዘ ዜና በአክሱም ከተማ ከ280 ሚሊዮን ብር በላይ በሚሆን ወጭ አዲስ የአስፓልት መንገድ ለመገንባት ስምምነት ተደርጓል። ስምምነቱን ያደረጉት የከተማው አስተዳደርና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ድርጅት ናቸው። የከተማው ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካህሳይ እንዳሉት የሚገነባው 13 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ "የግንባታ ወጭ በከተማው አስተዳደር የሚሸፈን ነው" ያሉት ከንቲባው ግንባታው በጊዜ ገደቡ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ደጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል ። የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ድርጅትን በመወከል ስምምነት የፈረሙት በድርጅቱ የአክሱምና አከባቢው ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ወንድወሰን ስዩም በበኩላቸው ለግንባታው የሚሆን ግብአት የማምረትና ማሽነሪዎችን ወደ ከተማው የማስገባት ሥራ ተጀምሯል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ የአስፋልት መንገዱ  ግንባታ ሥራ የፊታችን መስከረም ይጀመራል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም