በአሶሳ ከተማ ኮሮናን በመከላከሉ በኩል በመንግስት ተቋማት የሚታየው መዘናጋት ሊስተካከል እንደሚገባ ተመለከተ

52

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 23/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በሚገኙ የመንግስት ተቋማት ኮሮና ቫይረስን በመከላከል በኩል የሚታየው መዘናጋት ሊስተካከል እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የቫይረሱ መከላከል የቅስቀሳ መድረክ በአሶሳ ተካሂዷል፡፡

ከመድረኩ ተሳታዎች መካከል አቶ አብዱራህማን መሃመድ እንዳሉት፤ በአሶሳ ከተማ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት ቫይረሱን መከላከል የጤና ጽሕፈት ቤት ብቻ አድርገው ይመለከታሉ፡፡

በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ የእጅ መታጠብ አገልግሎት አቁመዋል ብለዋል፡፡

መዘናጋቱ በዚህ ከቀጠለ ቫይረሱ ከመከላከል ደረጃ አልፎ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ይገርማል ሳለው በበኩላቸው መዘናጋቱ በመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በከተማው ታክሲ አሽከርካሪዎች እና ተገልጋዮች ዘንድ ጭምር እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡

ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ  የመንግስት ተቋማት እና ግለሰቦች ጥንቃቄ እንዳለ ያመለከቱት ተሳታፊው ለመከላከሉ አስተዋጽኦ የሚያደርጉትን በመሸለም የሚዘናጉትን ደግሞ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስልግ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከፍተኛ አመራሩ በመድረክ ከማውራት ባለፈ በተግባር ምሳሌ ሆኖ መገኘት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

መንግስታዊ ተቋማት ያቋረጡትን እጅ መታጠብ እንደገና በመጀመር ለመከላከሉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ አቶ እንድሪሰ ቡሽራ ናቸው።

በመድረኩ የኩርሙክ ወረዳ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ቫይረሱን በመከላከል ያለው  ተሞክሮ በምሳሌነት ተጠቅሷል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ፈቃዱ ረጋሳ  የኮሮና  መከላከል ፕሮቶኮል የእያንዳንዱ ተቋም አመራር እና ሠራተኛ ምን ማከናወን እንዳለበት በግልጽ መቀመጡን ገልጸዋል።

በአፈጻጸም ረገድ ሁላችንም ከፍተኛ ችግር አለብን ብለዋል፡፡

በተለይ በከተማ በትራንስፖርት አግልግሎት ዘርፍ ቫይረሱን በመከላከል የሚታየውን መዘናጋት ለማስቆም የተደረገው ጥረት ጉዳዩ የሚመለከታው ተቋማት ስራውን ከጥቅም ጋር በማገናኝት ፈቃደኛ አለመሆን እንደሚስተዋል ጠቁመዋል፡፡

ቢሮው ችግሩን ለመፍታት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመቀናጀት በተለይ በመንግስት ተቋማት ድንገተኛ ቁጥጥር እንደሚጀምር ሃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ይህም በቫይረሱ መከላከል ላይ ትኩረት የሰጡትን በማበረታታት እና የሚዘናጉትን ደግሞ በማስተካከል  ወረርሽኙን  ለመግታት እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡

በተለይ የተቋማት አመራሮች ራሳቸውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የወጣውን  ፕሮተኮል ከመተግባር አንጻር ሊመዝኑ እንደሚገባ አቶ ፈቃዱ ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ከ50 የሚበልጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም