መንታ መንገደኞቹ

120

ገዛኸኝ ደገፉ /ኢዜአ/

የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ በሰሞኑ ወደ ስድስት የአፍሪካ ሀገራት ያቀኑት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የግብጽን አቋም በማስተዋወቅ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኒጀር፣ ኮሞሮስ እና ቱኒዚያን አዳርሰዋል። እነዚህ ሀገራት የተመረጡት ባላቸው ሚናና ተልእኮ ሲሆን ኬንያ፣ ኒጄር እና ቱኒዚያ  የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሀገራት ሲሆኑ ደቡብ አፍሪካ ድርድሩን ስትመራ በመቆየቷ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደተጠቀሱት ሀገራት ጉዞ ያደረጉት በኮንጎ ኪንሻሳ የኢትዮጵያ፣ የግብጽ እና የሱዳን የውሃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አካሂደው ያለውጤት ከተለያዩ በኋላ ነው። ከዚህ ስብሰባ በኋላ ግብጽ የህዳሴው ግድብ ድርድር ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ እየሰራች ሲሆን የአፍሪካ ህብረትን እንደመጠባበቂያ ለመጠቀም ሙከራ በማድረግ ላይ ትገኛለች። 

ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት እንደ ታንዛንያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ፣ ኒጀር አልጄሪያ አለፍ ሲልም በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጉብኝት ያደረጉት የግብጽ ባለስልጣናት ውጤቱ እስካሁን በግልጽ ባይታይም በቅርቡ ኡጋንዳንና ብሩንዲን በወታደራዊ ስምምነት ማእቀፍ  ውስጥ  ለማስገባት መሞከራቸው  የሚታወስ  ነው። 

ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት መሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ምንም መፍትሔ  አላመጣም  በሚል  ጉዳዩን ወደ  ጸጥታው  ምክር ቤት ለመውሰድ  ከፍተኛ  ግፊት ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።  ሁለቱ ሀገራት በዚህ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ተገናኝተው ምክክር አድርገዋል። በተለይ ግብጽ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የህዳሴው ግድብ ድርድር መፍትሔ ያስገኛል የሚል እምነት የላትም። ሁለቱ ሀገራት በኪንሻሳው መድረክ ካቀረቧቸው ሃሳቦች መካከል አንዱ ድርድሩ ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና አሜሪካ እኩል ሚና እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነበር። ይህ አካሄድ የአፍሪካ ህብረትን ሚና የሚያሳንስ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ መደረጉ ይታወሳል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት ሁለቱ ሀገራት የያዙት አቋም በአፍሪካ እምነት የለንም፣ ሂደቱም በአፍሪካ እንዲሳካ አንፈልግም፣ ለአፍሪካ ህብረትም አክብሮት የለንም እንደማለት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ግብጽ በአንድ በኩል የህዳሴው ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት በማውጣት ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ በሌላ በኩል ደግሞ የአፍሪካ ሀገራትን ለማግባባት መንታ ጉዞ ላይ ትገኛለች። ሦስቱ አገራት  ከግድቡ ጋር በተያያዘ አቋማቸውን ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት በደብዳቤ ያሳወቁ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል የተያዘው አቋም ድርድሩ አሁንም በአፍሪካ ህብረት እንዲቀጥል ነው። በየጊዜው የተለያየ አቋም የምታሳየው ሱዳን ከሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት አለመግባባቶችን ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት እውቅና እሰጣለሁ ማለት ጀምራለች። የአሁኑ አቋሟ ምን ያህል የሚዘልቅ ስለመሆኑ ለጊዜው ባይታወቅም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ወደ አራት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ዴሞክራቲክ ሪፐብለክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ እንደሚጓዙ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ግብጽ የህዳሴው ግድብ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ወደ ተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ለመውሰድ ለጀመረችው እንቅስቃሴ ተስፋ ያስቆረጣት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በግብፅ ካይሮ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው። ሰርጌ ላቭሮቭ ከግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ጋር ተገናኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በግብጽ በኩል ከተጠበቀው በተቃራኒ የአፍሪካ ኀብረትን የአደራዳሪነት ሚና አጉልተዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የሚደረጉ ድርድሮች በሶስቱ የወንዙ ተጋሪ ሀገራት ብቻ መሆን እንዳለበትም የሀገራቸውን አቋም ግልጽ አድርገዋል።

የግብጽ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ከራሷ በሚነጭ ወንዝ እና በራሷ ሀብት የገነባችውን የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት “የእኛ ይሁንታ የሌለበት ከሆነ አደጋው የከፋ ይሆናል” በማለት በየጊዜው ሲያሰሙ ሰነባብተዋል። የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በቅርቡ በመገናኛ ብዙሀን ባሰሙት ንግግር ከግብፅ የውኃ ድርሻ አንዲት ጠብታ መንካት አይቻልም፣ ይሄ ከሆነ ቀጠናው ወደማይታሰብ አለመረጋጋት ይገባል የአባይ ውሃ የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ቀይ መስመር ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በግብጽ በኩል የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል የባዘኑበት ጊዜ ባይኖርም የግድቡ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ጊዜው እየተቃረበ ሲመጣ ግን በሀገር ውስጥ ጉዳይ ስውር እጃቸው እስከመስረዘም የደረሰ ዘመቻ መክፈታቸው እየታየ መጥቷል።  

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ ሰሞኑን ለሀገሪቱ ፓርላማ የአፍሪካ ጉዳዮች ኮሚቴ በሰጡት ማብራሪያ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በግብጽ ላይ ጉዳት እንደማያስከትል ገልጸው ነበር። ሳሚ ሽኩሪ በሚመጣው ክረምት ከተለመደው በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅ በመጠቆም ኢትዮጵያ የሁለተኛ ዙር ሙሌት ብታከናውን ግብጽ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ አለመኖሩን ይልቁንም ጎርፉ የአስዋን ግድብን በመሙላት ግብጽ ተጨማሪ ውሃ እንድታገኝ እድል ይሰጣታል በማለት ነበር የተናገሩት። ምንም እንኳ የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽንና ሱዳንን የማይጎዳ መሆኑን ጠንቅቀው ቢገነዘቡም ግድቡ የኢትዮጵያን ተጽእኖ ፈጣሪነት ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ እየተጠናቀቀ ሲመጣ እንቅልፍ ነስቷቸዋል።

ትኩረቱን በአካባቢያዊ ሰላምና ደህንነት ላይ ያደረገው ጂኦ ፖሊቲካል ፊውቸር የተባለው የአሜሪካ የጥናት ተቋም በቅርቡ ባወጣው ትንታኔ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢትዮጵያ የግድቡን ከፍታም ሆነ ውሃ የመያዝ አቅም ትቀንሳለች ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ብሏል። የተቋሙ ተመራማሪ ሂላል ክሃሻን ኢትዮጵያውን ያላቸውን ሁሉ እየከፈሉበት ያለው የግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያ ልማት የማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን ማሳያ መሆኑን ጠቁመው ይሄንን እውነታ የግብጽና የሱዳን ፖለቲከኞች ሊቀበሉት አልወደዱም በማለት ነበር የገለጹት።

የኬንያው ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ ግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የምታራምደው አቋም ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የግድቡን ግንባታ የሚደግፉ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም ያስቆጣ ተግባር ስለመሆኑ በርእሰ አንቀጹ አስነብቧል። ጋዜጣው የናይል ወንዝ የአስራ አንዱ የተፋሰሱ ሃገራት የጋራ ንብረት መሆኑን አፅንኦት በሰጠበት ርእሰ አንቀጹ ሱዳንና ግብፅ የህዳሴው ግድብ በሚመለከት የጦርነት ነጋሪት ከመምታት በመቆጠብ አለመግባባቱን በስምምነት መፍታት አለባቸው ብሏል። 

ግብፅ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለዘመናት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ እንደቆየች የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። አንዳንድ ጽሑፎች እንደሚጠቀሙት ባለፉት ሃምሳ አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠሩ ችግሮች ግብጽ ያልተሳተፈችበት አለመኖሩን ነው። በተለይ በደርግ ዘመን የነበረው የ17 አመታት የእርስ በእርስ ግጭት፣ የኢትዮ- ሶማሊያ እና ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነቶች ወቅት በተቃውሞ የሚንቀሳቀሱትን በእጅ አዙር ስትደግፍ እንደነበር ይነገራል። ከቅርብ ጊዜያት ክስተቶች መካከል ደግሞ በትግራይ ክልል ከተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት ግጭቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የግብጽ እጅ ስለመኖሩ ብዙዎች ይገልጻሉ። በተለይ የህዳሴው ግድብ የሚገኝበት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ትኩረት ማድረግ ጀምረዋል። 

ይህ ወቅት ኢትዮጵያ የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን እየሰራች የምትገኝበት ወሳኝ ወቅት ነው። ይህን ወሳኝ ምእራፍ ለማደናቀፍ ግብጽም ይሁን ሱዳን ያለእረፍት እየሰሩ ይገኛል። በተለይ ግብጽ የውሃ ሙሌቱ እንዳይሳካ ለማድረግ የመጨረሻ ካርዷን አውጥታ እየተወተች ትገኛለች። በውስጥም ይሁን በውጭ በኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር የማትገባበት ስፍራ የለም። በውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶች የዚሁ እንቅስቃሴ ማሳያ ናቸው። እናም ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም ይልቅ በህብረት የምንቆምበትና ታሪክ የምንሰራበት ወቅት ላይ በመሆናችን የውስጥ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ማናቸውም ክስተቶች ምንጫቸውና ዓላማቸው ልንገነዘብ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም