የግል ትምህርት ቤቶች ሊመዘኑ ይገባል- የትምህት ዘርፍ አመራሮች

60
ሐምሌ 25/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የሚያካሂደውን ምዘና ወደ ግል ትምህርት ቤቶችም ሊያሰፋው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች ተናገሩ፡፡ ትምህርት ቢሮው በበኩሉ በሰው ኃይል እጥረት ምክንያት የግል ትምህርት ቤቶችን መመዘን እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አስር ስርዓተ ትምህርት ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ከበደ እንዳሉት ትምህር ቢሮው በየዓመቱ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚያካሂደው ምዘና በትምህርት ቤቶቹ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመለየትና ለመፍታት እገዛ እያደረገ ነው፡፡ በየትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማትና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች እጥረቶች እንዲቃለሉ በማድረግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ነው አቶ ተሾመ ያብራሩት፡፡ ይሁን እንጂ ምዘናው የሚካሔደው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ብቻ በመሆኑ በመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ያለውን ልዩነት ለመረዳት እንዳልተቻለ ነው የገለጹት፡፡ አቶ ተሾመ እንዳሉት የግል ትምህርት ቤቶችም በምዘናው ቢካተቱ በትምህርት ቤቶቹ መካከል የፉክክር መንፈስን በማጎልበት ለትምሀርት ጥራት መረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ስርዓተ ትምህርት ክትትል ቡድን መሪው ሰይፉ ፍስሃም ምዘናው በትምሀርት ቤቶች ብቻ ሳይሆን በመምህራንና በተማሪዎች መካከል የፉክክር መንፈስን እንደሚያዳብር ገልጸዋል፡፡ ምዘናው የታለመለትን ግብ እንዲመታ የመዛኞችን አቅም የማጎልበት ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸው ትምህርት ቤቶችም ለመመዘን የሚያበቋውን መረጃዎች በሰዓቱ ማቅረብ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የለውጥና አጠቃላይ ሪፎርም የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በለጠ ንጉሴ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን የመመዘኑና እውቅና የመስጠቱ ስራ ከተጀመረ ሰባት ዓመት መቆጠሩን አስታውሰው በዚህ ዓመትም 559 ትምህርት ቤቶች እየተመዘኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ምዘናው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ በመሆኑም በስራው ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ ምዘናውን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችን በምዘናው የማካተት እቅድ መኖሩን ገልጸው አሁን ያለው አደረጃጀትና የሰው ኃይል እጥረቱ ምዘናውን ለማድረግ እንቅፋት እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም