ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር 2ኛ ድሉን በማስመዝገብ 9ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቀቀ

76

ሚያዚያ 20/2013 (ኢዜአ) ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ሁለተኛ ድሉን በማስመዝገብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ከሚያዚያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በቱኒዚያ እየተካሄደ የሚገኘው 32ኛው የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ዛሬም ቀጥሎ ውሏል።

በውድድሩ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ መሆኑ ይታወቃል።

ዛሬ ዘጠነኛና አስረኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ በተደረገው ጨዋታ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የኮትዲቯሩን አሴክ ሚሞሳስን በአምስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 2 አሸንፏል።

ውጤቱን ተከትሎም ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በመጀመሪያ የውድድሩ ተሳትፎ ዘጠነኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከ2 ለ 0 መመራት ተነስቶ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻለ ሲሆን በውድድሩም ሁለተኛ ድሉን ማስመዘገብ ችሏል።

በተመሳሳይ በአፍሪካ የሴቶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከ5ኛ እስከ 8ኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ዛሬ ከኬንያው ኬንያ ፓይፕላንስ ጋር ባደረገው ጨዋታ በሶስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 ተሸንፏል።

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በውድድሩ አምስተኛ ወይም ስድስተኛ ደረጃን የማግኘት እድሉን ያጣ ሲሆን ነገ ሰባተኛ ወይም ስምንተኛ ደረጃን ለማግኘት ከቡርኪናፋሶው ዱዋኔስ ክለብ ጋር ይጫወታል።

የአፍሪካ የሴቶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን የሚካሄዱ ሲሆን የቱኒዚያው ካርቴጅ ከኬንያው ኬንያ ፕሪዝንስ እንዲሁም ሌላው የቱኒዚያ ክለብ ሲኤስ ሰፋክሲያን ከናይጄሪያው ከስተምስ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።

32ኛው የአፍሪካ የሴቶች የቮሊቦል ክለቦች ውድድር ከነገ በስቲያ ይጠናቀቃል።

በተመሳሳይ በቱኒዚያ በተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ የወንዶች ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው ወላይታ ዲቻ ውደድሩን በ15 ደረጃ ማጠናቀቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም