በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ዶክተር ነኝ በማለት ሲያጭበረብር የተገኘ ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

66

ጎባ ሚያዝያ 20/2013 (ኢዜአ) የጎባ ወረዳ ፍርድ ቤት በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ዶክተር ነኝ በማለት በተደጋጋሚ ህብረተሰቡ ላይ የማጭበርበር ወንጀል ፈጽሟል ያለውን ግለሰብ በ6 ዓመት ከስድስት ወር እስራትና በገንዘብ ቀጣ።

የወረዳው ፍርድ ቤት ዛሬ ባዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በጎባ ከተማ ኦዳ በሃ ቀበሌ ነዋሪ በሆነው አብዱልጀዋድ አማን ላይ ነው ።

ግለሰቡ  በተደጋጋሚ በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ጊቢ ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች የደንብ ልብስ በመልበስ በሰራቸው የማጭበርበር ወንጀሎች መከሰሱ በችሎቱ ተመልክቷል ።

ግለሰቡ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ አራት ሰዓት አካባቢ በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ጊቢ ውስጥ አቶ አልይ ሶሞ የተባሉ የግል ተበዳይን "የተሻለ መድኃኒት በእኔ ክሊኒክ ውስጥ ይሸጣል" በማለት 3 ሺህ 460 ብር ተቀብሏቸው መሰወሩን ተበዳዩ ለፖሊስ በሰጡት ቃል መረጋገጡን  የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ተማም ጁንዲ በችሎቱ ላይ አሰምተዋል።

ግለሰቡ በተጨማሪም በተጠቀሰው ሆስፒታል ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ አቶ አህመድ አብዱላሂ የተሰኙ የግል ተበዳይን 8 ሺህ ብር ለመቀበል እያስማማ ባለበት ሁኔታ ማንነቱን ለማረጋገጥ ባደረጉት ጥረት ጥርጣሬ ስላደረባቸው ለጎባ ከተማ ፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እጅ ከፍንጅ መያዙን  ዳኛው አመልክተዋል

"ተከሳሽ በፖሊስ በተያዘበት ወቅት 18 ሲም ካርድ፣ ሁለት ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ቀፎዎችና 10ሺህ 630 ብር ኤግዚቢት ተገኝቶበታል" ብለዋል ዳኛው ።

ግለሰቡ ድርጊቱን አለመፈጸሙን ለፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል በመስጠት የቤተሰብ አሰተዳዳሪ እንደሆነም ገልጻል።

ግለሰቡ በተከሰሰበት ወንጀል አቃቤ ህግ ባቀረበው ማስረጃ መረጋገጡን የገለጸው ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓም ባዋለው ችሎት ሌሎችንም ያስተምራል በሚል በ6 ዓመት ከስድስት ወር እስራትና በ2 ሺህ ብር ገንዘብ እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ከፍርድ ውሳኔ በኋላ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር አቡበክር መሐመድ  ሆስፒታሉ ከባለሙያዎች የደንብ ልብስ አጠቃቀምና ከባጅ አደራረግ ጋር የሚስተዋሉ ጉድለቶችን እንደሚያጤኑ ተናግረዋል፡፡

ለወደፊቱ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት ዶክተር አቡበክር ህብረተሰቡም ከደረሰኝ ውጭ የሚደረጉ ክፍያዎችን እንዳይቀበልና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ከሆስፒታሉ ውጭ እንዲገዙ ሲታዘዙ ራሳቸው ብቻ ገዝተው እንዲያመጡ ምክራቸውን ለግሷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም