የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ወጣቱን ትውልድ ማዕከል ያደረገ ተግባራትን እየሰራ መሆኑ ገለጸ

238
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ  በስፔስ ሳይንስ አገሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወጣቱን ትውልድ ማዕከል ያደረገ  ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገለጸ። የስፔስ ሳይንሰ ሶሳይቲው በዘርፉ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ለማጠናከር ትናንት በአዲስ አበባ የዓለም ዘላቂ የአመራር ድርጅት ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ፈጽሟል። ስምምነቱም ሁለቱ ተቋማት በስፔስ ሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታከናውናቸውን ስራዎች ለመደገፍ መሆኑ ተገልጿል። በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የቦርድ ሊቀመንበር ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ሲቋቋም በአጠቃይ ለአገሪቱ እድገት እንዲያግዝ ታስቦ ሲሆን  በተለይ ወጣቱ በዘርፉ እንዲሰራ ብዙ ይጠበቅበታል። ካለፉት አስራ ሁለት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ በዘርፉ እየተሰራ ሲሆን በይበልጥ የተጀመሩትን ለማጠናከርና ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረስ ከአጋር ድርጅቱ ጋር ስምምነት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ በተለያዩ መስፈርቶችና የተዘጋጁ ፈተናዎችን በማለፍ ለልምድ ልውውጥ ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከነበሩት ሁለት ኢትዮጵያዊያን ውስጥ ዘሚካኤልን አነጋግረነው ስለጉዞው ገልጾልናል። ዘሚካኤል ሀብተገበየው ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ለአስራ አምስት ቀን ቆይታ ያደረገ ሲሆን በቆይታውም ብዙ ልምዶችን እንደቀሰመ ገልጿል። በዓለም ትልቁ የኢንጅነሪንግ ዩንቨርሲቲ የሚገኝበትን ቦስተንን መጎብኘቱም በቀጣይ ሊደርስበት ለሚያስበው ህልሙ እውን ለማድረግ ይበልጥ ጠንክሮ በትምህርቱ እንዲገፋበት መነሳሳትን እንደፈጠረለት ገልጿል። በቀጣይም ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ኢሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ለማጥናት እንደሚፈለግ ገልጾ፤ ይህም ዘርፍ በአገር ውስጥ ባለመኖሩ በውጭ እንደሚከታተልና ወደ ፊትም ይህ የትምህርት ዘርፍ በአገር ውስጥ እንዲጀመር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግሯል። የዓለም ዘላቂ የአመራር ድርጅት ተወካይ ሚስተር ፓውል ቦጋረዲት በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲና የእኛ ድርጅት ብዙ የጋራ ፍላጎቶች አሉን። በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ውስጥ የስፔስ ሳይንስ እድገት ትልቅ ድርሻ እንዳለው በማውሳት "አሁን በጀመርናቸው ስራዎች ከስፔስ ሳይንሰ ባሻገር የባህልና አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ትስስር እንዲኖር እንሰራለን" ብለዋል። ከኢትዮጵያ ተወክለው ከሄዱት ሁለቱ ተማሪዎች ባሻገር የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ከቻይና የተውጣጡና አሜሪካ የነበሩ ሲሆን ኢትዮጵያን ለመጎብኘትም በማዕከሉ ተገኝተዋል። የኢትዮጵያን ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ መሰል ተግባራትና የስፔስ ሳይንስ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ በቀጣይም ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ከአጋር ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ ገልጾ፤  መንግስትም ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል።                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም