ተሳትፎአዊ መስኖ ልማት….

470
በወንድማገኝ ሲሳይ/ኢዜአ/ በኢትየጵያ የግብርና ምርትን ለማሳደግና የአገሪቱን ሕዝብ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከተነደፉት ስትራቴጂዎች መካከል የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ በሀገሪቱ ከሚተገበሩት ፕሮግራሞች መካከል “የተሳትፏዊ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮግራም” አንዱ ነው። በግብርና እና እንስሳት ሃብት በሚኒስቴር አዘጋጅነት የዚህ ፕሮግራም  “የግብዓትና የምርት ግብይት ፎረም”  በቅርቡ በባቱ- ዝዋይ ከተማ ለአራት ቀናት ተካሂዷል። በዚህ ወቅት የፕሮግራሙ ከፍተኛ የአግሪቢዝነስ እስፔሻሊስት የሆኑትን ወይዘሮ ንግሥት ከበደን አነጋግሬያቸው ነበር። እሳቸው እንደሚሉት ፕሮግራሙ የተቀረጸው በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ክፍተት ባለባቸው አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ይዞታ ያለቸውን አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት በመድረስ በምግብ እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ነው። እንዲሁም ትርፍ አምርተውና የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸው የተሻለ ገቢ በማግኘት ኑሯቸው እንዲለወጥ ለማስቻል ጭምር ነው። የኘሮግራሙ ዋና ዓላማዎችም  የአየር  ንብረት ለውጥን በመዋጋት የምግብ ዋስትናን በማሻሻልና  የአርሶ አደሩን ገቢ መጨመር የሚያስችሉ ሥራዎችን በመተግበር የመስኖ ተጠቃሚዎችን የኑሮ ደረጀ በዘላቂነት መለወጥ መሆኑን ነው ያስረዱት። የገበያ ትስስርን፣ የሴቶችና ወጣቶችን ተሳታፊነትን ማጠናከር፣ በተፈጥሮ ሀብት ላይ የተጋረጡትን ችግሮች ለመግታትና ለብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ አየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት ዓላማ እንዳለው ጠቅሰዋል። እንደ ባለሞያዋ ገለፃ የኘሮግራሙን ዓላማ ከግብ ለማድረስ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት፣ የመስኖ ሥፍራዎችን ከመለየት አንስቶ በዲዛይንና በግንባታ እንዲሁም በሥራ እንቅስቃሴ (Operation) እና ጥገና (Maintenance) በቂ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ይደረጋል። ፕሮግራሙ በትግራይ ፣ በአማራ ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ  ክልሎች ውስጥ ባሉ የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው እና ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ 110 ወረዳወች ውስጥ  የሚተገበር ይሆናል። ፕሮግራሙ በሶስት ዋና ዋና የክፍሎች የሚመራ ሲሆን እነሱም የአነስተኛ መስኖ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ዘላቂ የግብርና ልማት እና የማናጅመንት፣ የክትትልና ግምገማ ስራዎች ናቸው። ይህ ፕሮግራም በሃገሪቱ ከ145 ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ ኑረዲን ኣሣሮ ናቸው። እንደሳቸው ገለፃ ፕሮግራሙ በ2009 ዓ.ም ታኅሣሥ ወር አጋማሽ ወዲህ የተጀመረ ሲሆን ለስድስት ዓመታት ይተገበራል። በነዚህ ጊዜያትም ከ150 በላይ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶች በተመረጡት ወረዳዎች እንደሚገነቡ አስታውቀዋል። በዚህም 18 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ በማልማት የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸውን 108 ሺ 750 አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮችን ጨምሮ ከ600 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህን እውን ለማድረግም ወንዞችን በመጥለፍ፣የከርሰ ምድር ውሃን በመቆፈርና ቆለማ አከባቢዎች ደግሞ ከደጋና ወይናደጋ አካባቢ የሚጥለውን ዝናብ ተከትሎ የሚመጣውን ጎርፍ በመያዝ ለመስኖ ልማቱ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። በፕሮግራሙ ቀጥታ ተጠቃሚ ለሆኑ ከ46 ሺህ በላይ አባወራዎች የመስኖ ኤክስቴንሽን አገልግሎት ስልጠና የመስጠት ፣የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች በዘላቂነት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸትና በግብይት የማስተሳሰር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ይገልጻሉ። እስካሁን በፕሮግራሙ በተካሄደው እንቅስቃሴም ዝርዝር ጥናትና ዲዛይን ተሰርቶላቸው ግንባታቸው ከተጀመረው ከ50 በላይ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 20ዎቹ ተጠናቀዋል። በተጠናቀቁት የመስኖ እውታሮችም 3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑ 18 ሺህ አባወራዎች የተመረጡና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። እንደ አቶ ኑረዲን ገለፃ በዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድና በኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ ድጋፍ የሚካሄደው ፕሮግራም ዋና ዓላማ የገጠሩን ህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል፣የገቢ ምንጭ ማሳደና የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት ማረጋገጥ ነው። በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ኀብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙመድ  በዘልማዳዊ የግብይት አካሄድ መመራትና ግብርናን ቢዝነስ አድርጎ አለመስራት አነስተኛ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት እየጎዳው ይገኛል። የት ? መቼ ? ለማን ? በምን ያህል ዋጋ ? እንዴት መሸጥ አለብኝ ብሎ አዋጭነቱን ሂሳቡን ሰርቶ አቅዶ ያለመነሳት፣ የገበያ ትስስር የመፍጠር ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የህብረት ስራ ማህበራት ያለመጠናከርና አርሶ አደሩ  በተደራጀ መልኩ ግብይትን አለመምራቱም ሌላኛው ችግር መሆኑን አንስተዋል። ይህንን ችግር ከማቃለል አኳያ ፕሮግራሙ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በተለይ ገጠርን ማዕከል ያደረገ ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ልማትን ዕውን ለማድረግ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አለው። በመንግስትና በልማት አጋሮች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚገነቡ የመስኖ ተቋማትም ዘመናዊ የእርሻ ዘዴን ለማስፋፋት፣በቂና ጥራት ያለው ምርት ለማምረትና በወቅቱ ለገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩና ኀብረት ሥራ ማህበራት ከዘርፉ ሀብት እንዲያፈሩ ይረዳል ይላሉ። አቶ አብዲ እንዳሉት ከፕሮግራሙ የትኩረት መስኮች መካከል ከ68 ሺህ ሄክታር በላይ የተፋሰስ ልማትን ማካተቱ ልማትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያስችላል። ፕሮግራሙ ከሚካሄድባቸው አከባቢዎች መካከል በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን የሚገኘው የዘንገና የመስኖ ግበዓት አቅርቦትና ምርት ግብይት ዩኒዬን አንዱ ነው። የዩኒዬን ስራ አስኪያጅ አቶ ሐብታሙ አበራ በሰጡት አስተያየት ፕሮግራሙ የዩኒዬኑ አባል ለሆኑ 10 የኀብረት ሥራ ማህበራት አባላት ስልጠና በመስጠት፣የቢሮ ቁሳቁስ በማበርከትና ለግብይት መሳለጥ ድጋፍ አድርጓል። ይህም ዩኒየኑ ከጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ከእንጅባራ ዩኒቨርስቲ፣ከአዲስ አበባና ባሕርዳር የአትክልትና ፍራፍሬ ተጠቃሚዎች ጋር ያለውን የገበያ ትስስር ለማጠናከር ረድቶታል። ዩኒየኑ ከነዚህ ተቋማት ጋር ያለውን የገበያ ትስስር በማሳለጥ በ2011 በጀት ዓመት 240 ሺህ ብር የተጠራ ትርፍ ለማግኘት አቅዷል። የተሳትፏዊ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚደረግባቸው ክልሎች የመጡ አንዳንድ አስፈጻሚዎች በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲስፋፋና በተለይም ሴት አርሶ አደሮች በግልም ሆነ በቡድን ተጠቃሚ እንዲሆኑና የራሳቸውን ገቢ እንዲያሳድጉ ፕሮግራሙ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል። በፕሮግራሙ በዋነኛነት የተጠቃሚ አባወራዎች፣እማወራዎችና የልማት ሠራተኞችን አቅም ለማሳደግ የሥልጠና ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ለስራ የሚያስፈልጉ ማትሪያሎችና የትራንስፖርት መገልገያዎችም እያሟላ ነው። በተለይ የፕሮግራሙ ተሳተፊ አርሶ አደሮች በምግብ እራስን ከመቻል ባለፈ የተሻለ ገቢ አግኝተው በዘላቂነት ህይወታቸው ሊቀየር የሚችለው፤ በግብይት ሂደቱ ላይ የሚታዩ ችግሮች ሲቀረፍ ነው ያሉት  የመድረኩ ተሳታፊዎች በዚህ ዙሪያ በጋራ ተወያይተው የመፍትሄ ሀሳብ አስቀምጠዋል። በፕሮግራሙ በሚካሄድባቸው አራቱም ክልሎች እርስ በእርስ እየተማማሩ ለመሄድና በ2011 ዓ.ም ፕሮግራሙን አስፋፍተው ለማስፈጸምም እንደሚሰሩ አስምረውበታል። በግብይት ሂደት ሲተገበሩ ያጋጠሙ ማነቆዎች ውስጥ  በግብዓት ፍላጎት ዳሰሳ ወቅት ለዝናብ ሰብል እንጂ ለመስኖ ግብዓት ትኩረት ያለመስጠት፣ የተሸሻሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር አቅርቦት እጥረት ተጠቅሰዋል። የተሸሻሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮች የዋጋ ውድነት፣ ጸረ አረምና ጸረ ተባይ መድሀኒቶች ጥራት መጓደል እንዲሁም በሚፈለገው አይነትና መጠን ያለመገኘት እንዲሁ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም