ሁለተኛውን ዙር የኮሮና ክትባት መርሃ ግብር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

45

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 18/2013 /ኢዜአ/ ሁለተኛውን ዙር የኮሮና  የክትባት መርሃ ግብር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ስርጭት ለመከላከል መንግስት የተለያዩ የመከላከል እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል።

የኮቪድ መከላከያ ፕሮቶኮል በማዘጋጀት ዜጎች እንዲተገብሩ በማድረግ ስርጭቱን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

ለመከላከል የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ በኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ፍቃድ የተሰጣቸው አስትራዜኒካ እና የሳይኖ ፋርም ክትባቶችን በማስገባት ክትባት በመሰጠት ላይ ይገኛል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ሁለተኛውን ዙር የክትባት መርሃ ግብር ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው።

"ለዚህም 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን የክትባት ዶዝ ከለጋሽ አገራት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል" ያሉ ሲሆን፤ እስከ ህዳር 2014 ዓ.ም ድረስ 20 ሚሊዮን ክትባት ወደ ኢትዮጵያ የማስገባት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅድሚያ የሚሰጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ክትባቱን እያገኙ ሲሆን የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም እስካሁን 470 ሺህ ዜጎች ክትባቱን ወስደዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፣ በዕድሜ ከፍ ባለው የህብረተሰብ በኩል የመከተብ ፍላጎት ቢኖርም አንዳንድ የተዛቡ ግንዛቤዎች በክትባቱ ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና እየፈጠሩ ነው።

በተለይም ክትባቱን ከእምነት ጋር ማያያዝ ሌላው ፈተና መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን ችግሩን ለመፍታት የሚያግዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ አስረድተዋል።

የአስትራዜኒካ ክትባት ለደም መርጋትና ሌሎች የጤና እክሎች እንደሚዳርግ ተደርጎ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን መሰራጨቱን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች እስካሁን ያጋጠመ የጤና እክል አለመኖሩን አረጋግጠዋል። 

ክትባቱ በአሁኑ ወቅት ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ የጤና ባለሙያዎች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎችና ዕድሜያቸው ከ50 እስከ 60 ሆኖ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

"ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች ከተቀመጠው የዕድሜ ገደብ ውጪ ክትባቱ እየተሰጠ መሆኑን ለእኛም በሚደርሱ ጥቆማዎች አሉ" ያሉ ሲሆን ለእዚህም ተገቢው ክትትል ተደርጎ ከተገኘ ሚኒስቴሩ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል። 

የጤና ሚኒስቴር እስከ ትናንት ባጠናከረው መረጃ መሰረት 1ሺህ 10 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ወስጥ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከልም እስካሁ 3 ሺህ 551 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም