በነገሌ ከተማ ታዳጊዋን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

58
ነገሌ ሃምሌ 25/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ነገሌ ከተማ የ14 አመት ታዳጊዋን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል የተከሰሱ  አምስት ግለሰቦች ከ13 እስከ 14 አመት እስራት እንዲቀጡ የሊበን ወረዳ ፍርድ ቤት ወሰነ፡፡ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መርጊያ ዴከማ ለኢዜአ እንደገለፁት በግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ውሳኔው የተላለፈው ድርጊቱን መፈጸማቸውን ከአቀቢ ህግ በቀረበ የህክምና፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ነው፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ኑክሪ ኢሳቅ ታዳጊዋን አባብሎ በስልክ በመጥራት አምስተኛ ተከሳሽ ሁሴን መሀመድ ደግሞ አስገድዶ በመድፈር ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ''በድርጊቱ የተሳተፉት 2ኛ፣ 3ኛና 4ኛ ተከሳሾች አብዱከሪም መሀመድ፣ አብዲ ኑርና ሁሴን መሀመድ የወንጀሉ ተባባሪና የድርጊቱ ፈጻሚ ሆነው የተገኙ ናቸው'' ብለዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ትላንት በነገሌ ከተማ በዋለው ችሎች በከተማው ፖሊስና አቃቢ ህግ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የህክምና፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል፡፡ በዚሁ መሠረት አንደኛና አምስተኛ ተከሳሾች በ14 አመት፤ ሁለተኛ፣ ሦስተኛና አራተኛ ተከሳሾች ደግሞ በ13 አመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ የወንጀል ጉዳዩን ያጣሩት የነገሌ ከተማ ፖሊስ ምርመራ ክፍል ባለሙያ ምክትል ሳጂን ኢዳ ወያ ''ፍርድ ቤቱ በጥፋተኞቹ ላይ ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ ከፍተኛ የሚባልና ለሌሎችም አስተማሪ በሆነ መልኩ ስለሆነ ተገቢ ነው'' ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም