የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበር በፕሪቶሪያ ተመሰረተ

63
አዲስ አበባ ሀምሌ 25/2010 ለኢትዮጵያ ልማት፣ ዴሞክራሲና አንድነት የሚያግዝ የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበር በፕሪቶሪያ ተመስርቷል። በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ እና በልዩ ልዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጀቶች ውስጥ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያቅፍ የፕሮፌሽናሎች ማህበር ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም መመስረቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ማህበሩ ለኢትዮጵያ ልማት፣ ዴሞክራሲና አንድነት የሚያግዝ ሲሆን ምሁራኑም በጥናትና ምርምር እንዲሁም ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በመለዋወጥ የበኩላቸውን ማበርከት እንዲችሉ የሚሰራ ማህበር መሆኑን በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በማህበሩ ምስረታ በመገኘት "በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሀገራቸው ውስጥ ያለውን ሰላምና ዴሞክራሲ ለማረጋገጥ በአንድነትና በትብብር ሊሰሩ ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም የማህበሩ መመስረት ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋዕፆ እንደሚኖረው ገልጸዋል። የማህበሩ መስራች አባላት በበኩላቸው ኤምባሲው ለማህበሩ ምስረታ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም