በኢትዮጵያ አዲስ የኮቪድ-19 መመርሚያ ኪት ተመረተ

55

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15/2013(ኢዜአ)  አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ አዲስ የኮሮና ቫይረስ መመርሚያ ኪት አመረተ።

ኢንስቲትዩቱ ከአሜሪካው ኦሪገን የጤናና የሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪት በተሳካ ሁኔታ በአገር ውስጥ አምርቷል።

መሳሪያው የሰው አካል በሽታን ለመከላከል የሚያመነጨውን 'ሞሎኪውል' መመርመር የሚያስችል ነው።

ይህም በአገሪቷ የሚከናወነውን የቫይረሱን ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ ማካሄድ ያስችላል ተብሏል፡፡

በተጨማሪም መሳሪያው በአገር ውስጥ መመረቱ የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ረገድ እንደሚያግዝና በሕክምና ዘርፉ የአገሪቷን አቅም በማሳደግም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።

የመመርመሪያ ኪቱ በሶስት መንገድ ቫይረሱን ለመመርመር እንደሚያስችል መሳሪያውን በማምረት ሂደት የተሳተፉት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ ዶክተር ተስፋዬ ገላናው ተናግረዋል።

ዶክተር ተስፋዬ የመመርመሪያ ኪቱ "ስኬት" የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

ኪቱ በአንድ ጊዜ ብዙ ናሙናዎችን መመርመር መቻሉም ከሌሎች ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

መሳሪያው የቫይረሱን ምልክት የሚያሳዩትንም ሆነ የማያሳዩትን ሰዎች ለመመርመርና ለመለየት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።

ምርመራው በዋናነት ከደም፣ ከምራቅና ከአፍንጫ ፈሳሽ በመውሰድ የሚሰራ ነው ብለዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ በበኩላቸው መሳሪያው የሰው አካል በሽታን ለመከላከል የሚያመነጨውን 'ሞሎኪውል' መመርመርና የበሽታውን ስርጭት ማወቅ ያስችላል ብለዋል።

ከኮቪድ-19 ቫይረስ በተጨማሪ ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመመርመርም ይውላል ብለዋል።

መሳሪያውን በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ ለማዋል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ እንደሆነም ተናግረዋል።

መሳሪያው በኢንስቲትዩቱና በኦሮሚያ ጤና ቢሮ ትብብር ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተመረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

መሳሪያው ከኢኒስቲትዩቱ ጋር በጥምረት እንዲሰራ በአሜሪካ የተለያዩ ምሁራን ያስተባበሩትና የብሪትሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶክተር በረከት ያዕቆብ ይህ ውጤት እንዲመጣ የአቅም ግንባታና ሌሎች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

በአገሪቷ የተመረተው ኪት ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም