ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ጠንካራ ሥራ መስራቷ ተገለፀ

149
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ጠንካራ ሥራ መስራቷን በአፍሪካ ህብረት ታላቅ የአረንጓዴ ከለላ ፕሮግራም አስተባባሪ ኤልቪስ ፓውል ታንገም ተናገሩ። ፕሮግራሙ የተራቆተ መሬትን በዕጽዋት ለመሸፈን የሚሰራ ነው። ፕሮግራሙ እኤአ በ2007 የተጀመረ ሲሆን ዓላማው በሰሃራ፣ በአትላንቲክ፣ በሴኔጋል አድርጎ እስከ ጂቡቲ ድረስ የሚዘልቅ 8ሺህ ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የዛፎች መስመር መዘርጋት ነው። የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስትታት ድርጅት (ተመድ) የመሬት መራቆት መከላከል ኮንቬንሽን በጋራ በመተባበር በታላቅ የአረንጓዴ ከለላ ፕሮግራም ላይ የሚሰራ ዘጋቢ ፊልምን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ በአዲስ አበባ ተሰጥተዋል። ታላቅ የአረንጓዴ ከለላ ፕሮግራም አስተባባሪ ኤልቪስ ታንገም እንደገለፁት፤ ከህብረቱ የ2063 አጀንዳ አካል የሆነው የአረንጓዴ ከለላ ፕሮግራም በአፍሪካ አገሮች ተቀባይነት እያገኘ ነው። ፕሮግራሙ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ20 የአህጉሩ አገሮች ተግባራዊ እየሆነ ሲሆን በደቡብ የአህጉሩ ክፍል የሚገኙ አገሮችም ጥቅሙን በመገንዘብ ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየታቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል። ፕሮግራሙን ተግባራዊ ካደረጉ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ጠንካራ ሥራ መስራቷን ተናግረዋል። በዚህ መሰረት ከ15 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት የአገሪቱ አካባቢ በማገገም ላይ ይገኛል ሲሉ ለአብነት ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ስኬት ለሌሎች አገሮች አስተማሪ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አስተባባሪው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ማሊ እና ኒጀርም መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን መልሶ እንዲያገግም የተሻለ ሥራ መስራታቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በፕሮግራሙ አማካኝነት የመጣውን ለውጥ ለማስተዋወቅና መነሳሳት ለመፍጠር ዘጋቢ ፊልምና የሙዚቃ አልበም እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ፊልምና የሙዚቃ አልበሙ የሚሰራው በአረንጓዴ ልማት የተራቆተ መሬትን መልሶ እንዲያገግም እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በማስተዋወቅ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ የሚደረግ ሥራን ለማነቃቃት ያለመ መሆኑን አስተባባሪው ይናገራሉ። የመሬት መራቆትን የመከላከል ሥራን ለማነቃቃት ከኢትዮጵያዊቷ አርቲስት ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ጋር በመሆን አልበም እየሰራች ያለችው ማሊያዊቷ አርቲስት ኢና ሞጃ (INNA MODJA) በጋዜጣዊ መግለጫው ተገኝታ የአልበም ስራውን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥታለች። በጋዜጣዊ መግለጫው የተሳተፈችው ኢትዮጵያዊት የአፍሪካ ወጣት ተመራማሪዎች ኮንቬንሽን አስተባባሪ ወጣት ወንጌል አበበ ''ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ የበኩላችን እንወጣለን'' ብላለች። ወጣት ተመራማሪዎች ኮንቬንሽንም በቅርቡ በሚያካሂደው ጉባኤ አርቲስቶችና ሙዚቀኞች ፕሮግራሙን በማስተዋወቅ የሚቻላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚሰሩ መሆናቸውን ገልጻለች። የመሬት መራቆት የመከላከል ሥራው የአህጉሪቱን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ተብሏል። በዚህ ረገድ በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያ የተሰሩ ሥራዎችን ጨምሮ በዘርፉ በተሰሩ ሥራዎች የ15 ሚሊዮን ዜጎችን ህይወት ማሻሻል መቻሉን ተገልጿል። ይሁን እንጂ የገንዘብ እጥረትና የአመለካከት ክፍተቶች በፕሮግራሙ ስኬታማነት ትልቅ ተፅእኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም