የአንበጣ መንጋ በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ማደረጉን ግብርና ሚንስቴር አስታወቀ

78

ሚያዚያ 14/2013 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ማደረጉን ግብርና ሚንስቴር አስታወቀ።

ከ25 ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው የተባለለት የበረሃ አንበጣ ላለፉት በርካታ ወራት ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ ቆይቷል።

ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ አንበጣን የመቆጣጠር ስራ ሲሰራ ቢቆይም ከመስከረም 2013 ዓ.ም ጀምሮ መነሻውን ከየመንና ሱማሌ ላንድ አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ጉዳት አድርሷል።

መንጋው ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ እና ሶማሊያን ክፉኛ ጎድቶም አልፏል።

በግብርና ሚንስቴር የእጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ቀደም ካለው ተሞክሮ በመነሳት አሁንም ተከስቶ ጉዳት እንዳያስከትል በተደራጀ መልኩ ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

የአንበጣ መንጋው በመኸር ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማደረጉን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተጠናከረ የመከላከል ስራ በመሰራቱ እና ወቅቱ ለመፈልፈል ምቹ ባለመሆኑ ስርጭቱ እየቀነሰ መምጣቱን የተናገሩት አቶ በላይነህ ከአጎራባች አገራት ይገባ የነበረው የአንበጣ መንጋም ቀንሷል ብለዋል።

በእድገት ደረጃው እንቁላል መጣል የጀመረ ቢኖርም እንዳይራባ ለማድረግ የተጠናከረ የቁጥጥርና አሰሳ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመከላከሉ ሂደት የባለሙያዎችን አቅም ከማሳደግ ጀምሮ በርካታ ስራዎች ሲሰራ እንደነበር ጠቁመው ካለፈው አመት ዝግጅት አንጻር ሲታይም አሁን ላይ የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል።

በኬሚካል ርጭት ወቅት ሲያጋጥም የነበረው የባለሙያዎች አልባሳት እጥረትም ተወግዶ በበቂ ሁኔታ እንድሟላ መደረጉን አንስተዋል።

በሚጠረጠሩ ቦታዎች በአውሮፕላን ቅኝት እየተደረገ መሆኑንና በተለይም ኪስ ቦታዎች ላይ ደግሞ ሄሊኮፕተር በመጠቀም አሰሳ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ አምስት ክልሎችና በድሬዳዋና አካባቢው ቀደም ሲል ተከስቶ በነበረው የአንበጣ መንጋ 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ላይ ጉዳት አድርሶ አልፏል።

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው አባ ወራዎች እና እማ ወራዎች የዘር ወቅት ከመድረሱ በፊት ግብአት መሰራጨቱን ጠቅሰው በቀጣይ የዘር ሽፋኑን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካ መጠነ ሰፊ ሰብል ያወደመው የአንበጣ መንጋ ዳግም አንሰራርቶ ጉዳት እንዳያስከትል በትብብርና በቅንጅት የመከላከል ስራው መጠናከር እንዳለበት ይታመናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም