የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 39ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው

53
ድሬዳዋ ሀምሌ 24/2010 የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 5ኛ ዓመት 39ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአስተዳደሩ በገጠርና በከተማ በተሰሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ መምከር ጀምረዋል፡፡ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አብዱልሰላም መሀመድ እንዳሉት ዛሬ በተጀመረውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ አስፈጻሚው አካል በማህበራዊ፣ በምጣኔ ሃብትና በፖለቲካ መስኮች ያከናወኗቸው ተግባራት ይገመገማሉ። የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና የፍትህ አገልግሎቶች በስፋት ውይይት እንደሚደረግባቸውም ነው የገለጹት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆኑት የድሬዳዋ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲና የኦዲት ጽህፈት ቤት ሪፖርቶች ቀርበው በምክር ቤቱ አባላት ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ በጉባኤው ዘንድሮ በሁሉም ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች የተስተዋሉ ክፍተቶችን ለመድፈንና በአዲስ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አፈ-ጉባኤ አስታውቀዋል፡፡ ጉባኤው የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የ2010 ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በስፋት ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ በተጨማሪም የአስፈጻሚ አካት የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ የምክር ቤቱ አባላት ከተወያዩበት በኋላ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በነገው ዕለትም ጉባኤው በአስተዳደሩ መሪ ዕቅድና በጀት፣ በአስተዳደሩ መዋቅራዊ ፕላን የጊዜ ገደብ ማራዘመን እና በሹመቶች ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም