የህዝቡን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አዲስ የተሾሙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ

94
ሀዋሳ ሀምሌ 24/2010 በአገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማስቀጠል የህዝቡን ሰላምና አንድነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰሩ አዲስ የተሾሙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ፡፡ ከአዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር በቅርበት ሆነው በመስራት ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን ጥረት እንድሚያደርጉ አቶ ደሴ ዳልኬ ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተመረጡት አቶ ሚሊዮን ማቲያስ ለኢዜአ እንደገለጹት ወቅቱ ህዝቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ለውጥ ለማምጣት የተነሳበት ጊዜ በመሆኑ የህዝብ ፍላጎትን መነሻ በማድረግ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ ለክልሉ ህዝብ ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠትና ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ በማዳመጥ ተገቢ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራት የተጀመረው አገራዊ ለውጥ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ተከትሎ በተፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቄያቸው የመመለሱ ሥራ ትኩረት እንደሚሰጠውም አቶ ሚሊዮን አመልክተዋል። የህዝቡን ጥያቄ በህገመንግስቱ መሰረት ለመፍታትና አንድነቱ እየጠነከረ እንዲመጣ  ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ እንደሚሰራም አመልክተዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ህዝቡ ማንኛውንም ጥያቄ ህገመንግስቱን በተከተለና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብና በህገመንግስቱ የተረጋገጠለትን መብት በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል፡፡ በደቡብ ክልል ምክረ ቤት ስልጣናቸውን ለአቶ ሚሊዮን ማቲያስ ያስረከቡት አቶ ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው በክልሉ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠልና አሁን ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይ ለማድረግ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኃላፊነታቸውን በስኬት ይወጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት አቶ ደሴ፣ ለእዚህም ከርዕሰ መስተዳድሩ ጋር ተቀራርበው በመስራት ልምዳቸውን ለማካፈልና ውጤት ለማምጣት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል  ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም