ኦኤምኤን በሚሊኒየም አዳራሽ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊያካሂድ ነው

70
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ ም በሚሊኒየም አዳራሽ ለሚያካሂደው የምርቃትና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ዝግጅት ማጠናቀቁን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤሜኤን) አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ። አስተባባሪ ኮሚቴው ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የፊታችን እሁድ ለሚያካሂደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሲያደርግ የነበረውን ዝግጅት አጠናቋል። ሚዲያው በህዝብ አቅም የሚደገፍ ህዝብንም ማዕከል አድርጎ የሚሰራ መሆኑን የገለፀው ኮሚቴው ከካርድ ሽያጭ በተጨማሪ በስፖንሰርሺፕና ቃል በማስገባት ገቢ በማሰባሰብ ሂደት ላይ መሆኑን አስታውቋል። የአስተባባሪ ኮሚቴው ሊቀመንበር ኢንጂነር አየለ ደጋጋ እንዳሉት፤ በፕሮግራሙ 25 ሺህ ህዝብ ለማሳተፍ ታቅዶ የመግቢያ ቲኬት በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አማካኝነት የሚዲያው አድማጮች አሉበት በተባሉ ቦታዎች ተሰራጭቶ እየተሸጠ ይገኛል። መደበኛ ካርድ በ250 ቪአይፒ ደግሞ 3 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። በእለቱ እንግዶች ከአምስት ሰዓት ጀምሮ ቦታ ይይዛሉ የተባለ ሲሆን መርሃ ግብሩ 6 ሰዓት ላይ በይፋ ይጀመራል። በእለቱ መታደም የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ስርጭት ፕሮግራሙን ተከታትለው ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉም ተገልጿል። ታዳሚዎች ወደ አዳራሹ ሲመጡ ካርዱ ላይ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ደረሰኝ ማያያዝ እንደሚኖርባቸው ኮሚቴው ገልጿል። ተጨማሪ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ይሆን ዘንድ የኦኤምኤን ሎጎ ያረፈበት ቲሸርት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ በአዋሽ ባንክና በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እየተሸጠ ይገኛል። ሚዲያው በፖለቲካና ህግ ጉዳዮች ላይ ከማንኛውም ብሄርና ሃይማኖት ገለልተኛ ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚሰራ ተጠቁሟል። ሚዲያው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሚዲያዎች በተለየ መልኩ የራሱን የአቀራረብ ፎርማት ይዞ እንደሚመጣ አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል። በተለይ ፖለቲካንና ባህልን አስመልክቶ ዜናና ዜና ነክ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔ መስጠት ዋነኛ የሚዲያው መለያ መሆኑንም ገልፀዋል። በሚሊኒየም አዳራሽ በሚካሄደው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና የሚዲያው ዳይሬክተር አቶ ጃዋር መሃመድ ይታደሙበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል። የገቢ ማሰባሰቢያው ለአዲስ አበባ ኦኤምኤን ስራ ማስኬጃ ብቻ የሚውል ይሆናል ነው የተባለው። ሚዲያው ከኦሮምኛ በተጨማሪ በአማርኛና በኢንግሊዝኛ ቋንቋ እንደሚሰራም የተገለፀ ሲሆን በቀጣይ በክልሎች ቅርንጫፍ ለመክፈት ማቀዱንም ነው ኮሚቴው ያስታወቀው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም