በአባቶች መካከል እርቀ ሰላም መውረዱ በአገሪቱ አንድነትና ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል - ካህናት

114
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እርቀ ሰላም አውርደው ወደአንድነት መምጣታቸው ለቤተክርስቲያኗ እድገት ብቻ ሳይሆን በህዝቦች መካከል አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ጭምር የሚያግዝ መሆኑን ካህናት ገለፁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና አሜሪካ በሚኖሩት የቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል ለዓመታት የቆየውን አለመግባባት ለመፍታት በተደረገ ጥረት አባቶቹ ሰላም ለማውረድ እና ምእመኑን አንድ ሆነው ለማገልገል መስማማታቸው ይታወሳል። በጉዳዩ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው ካህናት በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኗን በመከፋፈል ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየው የእምነቱ አባቶች ቅራኔ መፈታቱ ለትውልዱ አንድነትንና ሰላምን ለማስተማር ያግዛል። በአባቶቹ መካከል አንድነት መምጣቱ የቤተክርስቲያኗን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት የሚያጎላና የትውልዱን መሰረት የሚያጠነክር እንደሆነም ካህናቱ ጨምረው ገልጸዋል። ቀሲስ መስፍን ጥኡመልሳን የተባሉ አባት እንደገለጹት፤ በአገር ውስጥና ውጭ ተብለው የሚጠሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋእዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶሶች ምእመኑን በጋራ ለማገልገል መወሰናቸው ለትውልዱ አንድነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማስተማር ያስችላል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ በአባቶች መካከል የተከሰተው ቅራኔ ተገቢነት ያልነበረው እንደሆነ የገለጹት ቀሲስ መስፍን አባቶቹ ወደ አንድነት መምጣታቸው የቤተክርስቲያኗን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት ለተተኪው ትውልድ ለማስተማር እንደሚያስችል ተናግረዋል። አባ ገብረህይወት ጌጡ የተባሉ ሌላ ካህን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የሁለቱ ሲኖዶስ ወደ አንድ መምጣት ለቤተክርስቲያኗ ብቻ ሳይሆን ለአገር ሰላምና እድገት ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ተግባሩ እግዚአብሔርን ጭምር የሚያስደሰት እንደሆነ ገልጸዋል። መምህር ለአለም ብርሃን የተባሉ አባት ደግሞ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ወደ አንድ መምጣት ቃለ ወንጌል ለማስተማርና የተሳሳተውን ለመመለስ አገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳ ገልጸዋል። ሊቀዲያቆን ዮሐንስ መኮንን የተባሉ አባት እንደሚሉት፤ የተፈጠረው አለመግባባት ላለፉት ዓመታት ቤተክርስቲያኗ መወጣት ያለባትን ኃላፊነት እንዳትወጣ እድርጓታል። አሁን በተፈጠረው እርቀ ሰላምና ምቹ ሁኔታ አማካኝነት ሁለቱ አባቶች ወደ ሥራ ሲገቡ አንድነትንና ሰላምን ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉም መክረዋል። የቆየው ልዩነት የቤተክርስቲያኗ አባቶችን፣ ሊቃውንቶችን፣ ካህናትንና ምእመናን መሪር ሀዘንና ለቅሶ ውስጥ የጨመረ ጉዳይ ነበረ ያሉት ደግሞ መሪጌታ በጽአ አማረ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ግን ለቤተክርስቲያኒቷ አንድነት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተደረገው ጥረት የሁሉንም ሃዘንና ለቅሶ ማበስ የቻለ እንደሆነ ገልጸዋል። እርቁ ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ሁሉም የቤተክርስቲያኒቷ አባቶች፣ ካህናትና ምእመና በጸሎት መትጋት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በአባቶቹ መካከል የወረደውን እርቀ ሰላም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና በብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ላይ በተለያየ ጊዜ ተላልፎ የነበረውን ቃለ ውግዘት ትናንት አንስቷል። በሰሜን አሜሪካ ሲኖሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ እና ሌሎች ብፁዓን ሊቀነ ጳጳሳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ደማቅ አቀባባል እንደሚደረግላቸውም መገለጹ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም