በሲዳማ ለትምህርት ብርሀን ምዘና መርሀግብር ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

145

ሀዋሳ፣ ሚያዝያ 11/2013 (ኢዜአ) በሲዳማ ክልል ተግባራዊ ለሚደረገው የትምህርት ብርሀን ምዘና መርሃ ግብር ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስገነዘበ።

በሲዳማ ክልል የሚካሄደው  ሀገር አቀፉ የትምህርት ምዘና  መርሀ-ግብር ይፋዊ ማስጀመሪያ መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በሪሶ በሰነ ስርአቱ ላይ  እንዳሉት በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት ሥርዐት ከተጀመረ 115 ዓመት ሆኖታል።

በተለይ በእምነት ተቋማት ውስጥ ይሰጥ ከነበረው ኢ-መደበኛ ትምህርት ባሻገር በተለያዩ ዘመናት የነበሩ መንግሥታት መሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርትን ለማስፋፋት ባደረጉት ጥረት  አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸውን አውስተዋል።

"ሆኖም በመሠረታዊ የመማር ምጣኔ ሲለካ ግን እስካሁን 51 ነጥብ 8  በመቶ ብቻ በመሆኑ ግማሽ የሚሆኑ ዜጎች ማንበብና መፀፍ የማይቹሉባት ሀገር ተብላ እንድተፈረጅ አድርጓል" ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለዚህ ፍረጃ ካበቋት ችግሮች መካከል በመሰረታዊ የጎልማሶች ትምህርት መርሀ-ግብር የተማሩ ሰዎች በሀገሪቱ የመማር ምጣኔ ቋት ውስጥ አለመካተታቸው በዋናነት ተጠቃሽ  መሆኑን አመልክተዋል።

ዛሬ ላይ በይፋ የተጀመረው  የትምህርት ብርሀን ምዘና መርሀ-ግብር በሀገሪቱ ያለውን የመማር ምጣኔን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

በመርሀ ግበሩ በተለያየ መንገድ የማንበብ ፣ መፃፍና ማስላት ችሎታ ያዳበሩ ዜጎችን በመመዘን ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ለሚያስመዘግቡ በመደበኛው ትምህርት ከሶስተኛ ወደ አራተኛ  ክፍል ከተሸጋገሩ ዜጎች ጋር የሚያስተካክላቸውን የእውቅና ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎች የተመዛኞች ምዝገባ እየተካሄደ እንደሚገኝና የምዘና ፈተናውም ከሚያዚያ 17 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም  እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

መርሀ-ግብሩ የክልሉን  የመማር ምጣኔን እንደሚያሳድገው የጠቆሙት አቶ በየነ ለስኬታማነቱ በክልሉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አስገንዘበዋል።

የአርቤጎና ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በየነ በላይነህ በሰጡት አስተያየት በወረዳው ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባር ተኮር መሠረታዊ የጎልማሶች ትምህርት በስፋት ሲሰጥ ቆይቷል።

በትምህርት መርሀ-ግብሩ በርካቶች ተጠቃሚ ቢሆኑም ከሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት ባለፈ የሚሰጣቸው ዕወቅናም ሆነ የትምህርት ደረጃ ባለመኖሩ ተነሳሽነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

"አሁን ላይ የተጀመረው የምዘና መርሀ ግብር ዜጎችን ለበለጠ ዕውቀትና ክህሎት እንዲተጉ ከማነሳሳቱም በላይ በሀገሪቱ የተማረ ተብሎ የሚፈረጅ የሰው ቁጥር በእጅጉ እንዲጨምር የሚያደርግ ነው" ብለዋል።

ለመርሀ ግብሩ ስኬት በወረዳው ባሉ የትምህርት መዋቅሮች አማካኝነት ሁሉም ማንበብ ፣ መጻፍና ማስላት የሚችል ዜጋ ተመዝግቦ እንዲመዘን የተጠናከረ ሥራ እንደሚሰራ  አስታውቀዋል።

የቦሪቻ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው በወረዳው በርካታ ማንበብ ፣ መፃፍና ማስላት የሚችሉ አርሶ አደሮችና የተለያዩ  የህብረተሰብ ክፍሎች  ቢኖሩም  ያልተማሩ ተብለው  መፈረጃቸውን ገልጸዋል።

ዜጎችን የምዘና መርሀ-ግብሩ ተጠቃሚ በማድረግ እንደ ሀገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት የአካባቢውን ሽማግሌዎች ፣ የሐይማኖት መሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

በመርሀ ግብሩ በይፋዊ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ ከክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የተውጣጡ አስተዳዳሪዎች ፣ የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም