በጎንደር ከተማ በሚካሄደው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ከ20ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ

57

ጎንደር፤ ሚያዚያ 11/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ በሚካሄደው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ20 ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የከተማዋ አስተዳደር ገለጸ፡፡

መርሃ ግብሩን ለሚያስፈፅሙ አካላት በተዘጋጀው የስልጠና መድረክ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ እንዳሉት፤ መርሃ ግብሩ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚተገበር ነው፡፡

በዚህም በከተማዋ አስተዳደር ከ20ሺህ በላይ አባወራዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተመልክቷል።

በአማራ ከልል በመርሃ ግብሩ ከታቀፉ 17 ከተሞች ጎንደር እንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ ዘንድሮ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በከተማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ችግሮቻቸውን በሚያቃልሉ የልማት ተግባራት በማሳተፍ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

ለመረሃ ግብሩ ውጤታማነት በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ትኩረት ሰጥተው መሰራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የሴፍቲኔት መርሃ ግብሩ በከተማው ሶስት ክፍለ ከተሞችንና ሰባት ቀበሌዎችን የሚያቅፍ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ናቸው።

አቅመ ደካሞች፤ አረጋውያን፤ አካል ጉዳተኞችና በልመና ህይወታቸውን የሚገፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸውን የሚደጉሙበት በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም የመስራት አቅም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ በአነስተኛ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ተሳታፊ በማድረግ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

በከተማ ጽዳትና ውበት፣ በቆሻሻ ማስወገድ፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጥገናና በጎርፍ መፋሰሻ ቦዮች ጠረጋ የልማት ስራዎች ተሳታፊ በማድረግ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙበት አሰራር እንደሚተገበር አመልክተዋል፡፡

በተያዘው ወር በሚጀመረው የሴፍቲኔት መርሃ ግብር ከሚሳተፉት 5ሺ አባወራዎች 800 ያህሉ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በተለያዩ የልማት ስራዎች ተሳታፊ በመሆን ድጋፉን የሚያገኙ ይሆናል ብለዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ለምለም አስፋው በሰጡት አስተያየት የሴፍቴኔት መርሃ ግብሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብተረተሰብ ክፍሎችን ህይወት የሚታደግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም