የዓለም ዘላቂ የአመራር ድርጅት ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንሰ ሶሳይቲ ጋር በትብብር ሊሰራ ነው

69
አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2010 በኢትዮጵያ ቀጣይ ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲመዘገብ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን የዓለም ዘላቂ የአመራር ድርጅት አስታወቀ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የድርጅቱን ዋና ዳይሬክተርና የኢትየጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲን የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። የዓለም ዘላቂ የአመራር ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ፖውል ቦጋርድት እንዳሉት በዓለም ላይ በስፔስ ሳይንስ ጥሩ ሥራ ለመሥራት ድርጅቱ ለዘርፉ ተመራማሪዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጣል። ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዘላቂ ልማት ግቦች ለማሳካት የአቅም ግንባታ ስልጠናና የማማከር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ከተመራማሪዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የገለጹት ሚስተር ፖውል በቀጣይም በቅንጅት ውጤታማ ሥራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ እንዳሉት ሳይንሱን በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት ለማስተዋወቅ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የድርጅቱ ድጋፍ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ወደፊት ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ ለምትገነባቸው ድርጅቶች ዜጎች በሙያቸው መሥራት እንዲችሉ ከድርጅቱ ጋር የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል። ድርጅቱ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ለሁለት ተማሪዎች የአጭር ጊዜ ስልጠና ዕድል እንዲያገኙ ያደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጇ በቀጣይም ለስምንት ተማሪዎች ነፃ የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ለመስጠት ቃል መግባቱን ተናግረዋል። በአቡነ ጎርጎሪዮስ ትምህርት ቤት የ 12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ወጣት ዘሚካኤል ዳምጠው በአሜሪካ ሎሳንጀለስ ከተማ የአጭር ጊዜ ስልጠና ከወሰዱት ሁለት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አንዱ ነው። ወጣቱ ከትምህርቱ ጎን ለጎን በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለሰባት ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግል ቆይቷል። ወጣት ዘሚካኤል እንዳለው ከዘላቂ ልማት ግቦች ውስጥ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ፈጠራ በሚለው ግብ ዘጠኝ ላይ በስፔስ ኢንዱስትሪ ላይ ጥናት አካሂዷል። ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን መሠረት በማድረግ ወጣቶች በጥናትና ምርምር ላይ በንቃት መሳተፍ እንደሚኖርባቸውም መክሯል። ወጣቶች ምንም ዓይነት እንቅፋት ቢገጥማቸው ከዓላማቸው ሳይደናቀፉ ራሳቸውን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ማበልጸግ እንዳለባቸውም አስተያየቱን ሰጥቷል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው ድርጅቱ በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ወጣቱን ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረጉ ለኢትዮጵያ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍና በስልጠናና ማማከር ዘርፍ ለሚያደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ኢትዮጵያን በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ለማሳደግ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውንም የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልጸዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም