በመስኖ ስንዴን የማምረት ጅምር ውጤታማና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በምርምር ለመደገፍ እየሰራሁ ነው

60

ጎባ ሚያዝያ 10/2013( ኢዜአ) ስንዴን በመስኖ የማምረት ጅምር ውጤታማና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በምርምር ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ ከዚህ በፊት ከምርምር ማዕከላት ከተለቀቁ የዳቦ፣ ፓስታና ማካሮኒ የስንዴ ዝሪያዎች መካከል በ24ቱ ላይ ለመስኖ እርሻ ተስማሚነታቸውን ለመለየት የማላመድና የማባዛት ስራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል፡፡

በሲናና የግብርና ምርምር ማዕከል የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምርምር የስራ ሂደት ባለቤት ተመራማሪ አቶ አማረ ቢፍቱ ለኢዜአ እንደገለጹት  መንግስት ስንዴን በመስኖ ለማልማት እያደረገ ያለውን ጥረት ማዕከሉ በምርምር ለመደገፍ እየሰራ ነው፡፡

እየተካሄደ ባለው ምርምር የዘር መጠን፣የማዳበሪያ ፍላጎትና መጠን፣የውኃ አጠቃቀም ስሌትና ሌሎች ተያያዥ የልየታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አመልክቷል፡፡

የሲናና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክትር አቶ መሐመድ በሪሶ በበኩላቸው "ማዕከሉ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች፣ የእንስሳት መኖና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ዓላማ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።

"መንግስት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት እያደረገ የሚገኘውን ጥረት በምርምር ለመደገፍ በሁለቱ የባሌ ዞኖችና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ውስጥ እያደረገ የሚገኘው የምርምር ስራዎች የዚሁ ጥረት አካል ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቶ መሐመድ እንዳሉት ማዕከሉ በምርምር ጣቢያው ላይ ለመስኖ ስንዴ ልማት ተስማሚ የሚሆኑ የስንዴ ዝርያዎችን ለመለየት እያደረገ ከሚገኘው ምርምር በተጓዳኝ ከ100 በሚበልጥ ማሳ ላይ ከዚህ በፊት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የስንዴ ዝርያዎችን በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እያባዛ ነው፡፡

በ1978 ዓ.ም የተቋቋመው ማእከሉ እስከ አሁን በሰብል ዝርያዎችና በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ ከ80 በላይ የሚሆኑ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚ ማድረሱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም