በመተከል በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በገበያ ስፍራዎች ግብይት ተጀምሯል

103

መተከል፣ ሚያዚያ 10/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን በተፈጠረው አንፃራዊ ሰላም በገበያ ስፍራዎች ማህበረሰቡ የጋራ ግብይት መጀመሩን ኢዜአ ያነጋገራቸው የግልግል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

በመተከል ዞን በነበረው የፀጥታ ችግር የጋራ የግብይት ስፍራዎች ከነበሩት መካከል የግልገል በለስ ከተማ የቅዳሜ ገበያ ጭር ብሎ ሰነባብቷል።

አሁን ላይ ግን የዞኑ የተቀናጀ ገብረሃይል በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር በሰራው ያላሰለሰ ጥረት አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት መጥቷል።

የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች በቅዳሜ ገበያ ተገናኝተው በመሸጥና በመሸመት ግብይታቸውን አካሂደዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የግልገል በለስ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እንዳሉት ሰላምና መረጋጋት እየተፈጠረ በመሆኑና በዓልም እየተቃረበ በመሆኑ ነዋሪው፣ አርሶ አደሩና ነጋደው ቅዳሜ ገበያ ላይ ተገበያይተዋል።

በአብሮነት የሚታወቀው አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶችና የሰላም እጦት ለግብይት እንኳን ፍራቻና ስጋት አሳድሮ መቆየቱን አንስተው አሁን ላይ ግን ተስፋ የሚሰጡ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል ብለዋል። 

ኮማንድ ፖስቱ ከተቋቋመ በኋላ ህዝብን ለማጋጨት የሚሰሩ ጠላቶች እንዲለያዩ በማድረግና የተጠናከረ የፀጥታ ስራ በማከናወን በአካባቢው አንፃራዊ ሰለም ማስፈኑን ተናግረዋል። 

በቀጣይም ህዝቡ ከስጋት ተላቆ ወደ ዘላቂ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ የተጀመረው ጥረት እንዲቀጥል ጠይቀዋል። 

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በበኩላቸው የመተከል ዞን ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። 

በህዝብ መካከል ፍፁም ጥላቻና ጥል የለም ወደ ፊትም አይኖርም ያሉት ኮሎኔሉ የተለያዩ አካላት የግጭት ሴራ እየከሸፈ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከጀርባ ያሉ የውጭ ኃይሎች እና የጁንታው ተላላኪዎች የችግሩ ሁሉ ምንጭ መሆናቸውን ገልጸው አሁን ላይ ተጋልጠዋል፤ ህዝቡም በአንፃራዊነት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሷል ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት።

ኮማንድ ፖስቱም በአካባቢው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ጥረቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል መስዋዕትነት እየከፈለ ጭምር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም