በህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤት እያመጡ ነው - አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ

79

ሚያዚያ 9 /2013 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤት እያመጡ መሆናቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች አማካሪና የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ገለጹ።

"ሁለንተናዊ አጋርነትና ትብብር በተፋሰስ ልማት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ዘላቂነት" በሚል መሪ ሃሳብ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ እንደተናገሩት፤ የግድቡን ግንባታ ለማጓተት ቢሰራም ኢትዮጵያ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነቷን ለዓለም ለማሳወቅ ጥረት እያደረገች ነው።

ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎችም ገለጻ በማድረግና ግንዛቤ በመፍጠር እውነታውን እንዲረዱና ከኢትየጰያ ጎን እንዲቆሙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን በግልፅ በማሳወቅ መንግስት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በጀመረው የዲፕሎማሲ ስራ ውጤት እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

''ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያደላትን ሀብት ከመጠቀም የሚያግዳት ነገር የለም'' ያሉት አምባሳደሩ፤ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሊት በስኬት እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ፣ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ በበኩላቸው “ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት ለመጠቀም የሚከለክላት ዓለም አቀፍ ህግም ሆነ ፖለቲካ የለም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን አጠናቃ ህብረተሰቡን ከድህነትና ጨለማ ማውጣት አማራጭ የሌለው ግዴታዋ እንጂ ቅንጦት አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግብጽና ሱዳንን ሴራ ለማክሸፍ መንግስት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የጀመረውን ዲፕሎማሲ አጠናክሮ መቀጠልና የግድቡን ግንባታ ማፋጠን እንዳለበትም አስተያየት ሰጥተዋል።

ሃገራቱ በብቸኝነትና የበላይነት ውሃውን ለመጠቀም ፍትሃዊ ያልሆነ ሃሳብ በማቅረብና ድርድሩን በማጓተት ግንባታውን ለማስተጓጎል ቢሰሩም መንግስት የያዘው ቁርጠኛ አቋም የሚበረታታ በመሆኑ ሁሉም መደገፍ እንዳለበት አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን በመያዝ ምክንያታዊና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማስጠበቅ የጀመረችውን የሰለጠነ አካሄድ አጠናክራ መቀጠል እንዳለባትም ፕሮፌሰር ያዕቆብ ተናግረዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር መንገሻ አየነ “የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጰያ ህዝብ አንድነቱንና ሰላሙን መጠበቅ ይኖርበታል” ብለዋል።ከድህነት ለመላቀቅና አለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ህዳሴ ግድቡ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም