ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያ ዓመታት የሕዝቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ ትርክቶችን ይነዙ ነበር - የውጭ አገራት ምሁራን

80

ሚያዚያ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) ህወሓት ወደ ስልጣን በመጣባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሕዝቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ ትርክቶችን ይነዙ እንደነበር የውጭ አገራት ምሁራን ተናገሩ፡፡

መቀመጫው በአሜሪካ የሆነው "ኢትዮጵያዊነት" ዓለም አቀፍ የሲቪክ ተቋም "በኢትዮጵያ አሁን ላሉ ቀውሶች የምዕራባዊያን ምላሽ የሚኖረው ውጤት" በሚል ርዕስ የዌቢናር መድረክ እያካሄደ ነው።

የኦክላሃማ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ፕሮፌሰር ቴዎዶር ሬስታል በህወሃት የመጀመሪያ የስልጣን ዓመታት በአገሪቷ እንደነበሩ በማስታወስ፤ "ቡድኑ ተቀናቃኝ ነው ያለውን የፖለቲካ አመራር ያለምንም ልዩነት ያስርና ያሰቃይ ነበር" ብለዋል፡፡

ለቡድኑ ስጋት ናቸው ያላቸውን የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን በማባረር የፖለቲካ እንቅስቃሴውን ለማፈን መሞከሩንም አስታውሰው፤ ህወሓት ከመነሻው ሰብዓዊነትን በመርገጥ፣ ዴሞክራሲን በማጨናገፍና ማንነትን በመጨፍለቅ የሚታወቅ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

"ህወሓት ታማኝ ተቃዋሚዎችን በመፈልፈልና እውነተኛ ተቀናቃኞችን በማሰርና በማሰቃየት ይታወቅ ነበር" ብለዋል፡

፡ቡድኑ በርካታ ግፎችና ወንጀሎችን የፈጸመ በመሆኑ ድርጊቱ የሚያስደንቅ አለመሆኑንም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ ባለፉት ተከታታይ ምርጫዎች ኮሮጆ በመስረቅና በማጭበርበር ይታወቅ እንደነበረም ነው የተናገሩት፡፡

የምርጫ ውጤቶች መጭበርበራቸውን ተከትሎ በተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት የወጡ በርካታ ሰዎች መገደላቸውም እንደማይዘነጋ ገልፀዋል፡፡

በአምስተርዳም ቪዩ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ፕሮፌሰርና ኢትዮጵያን የተመለከቱ በርካታ ጥናቶችን የሰሩት ፕሮፌሰር ጆን አቢንክ በበኩላቸው የሕገ መንግስቱ መግቢያ 'እኛ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች' በማለት ቢጀምርም በተግባር ግን ብሄሮችንና ብሄረሰቦችን በመጨቆንና ባሕላቸውን በመጨፍለቅ ይታወቅ ነበር ነው ያሉት፡፡

የቡድኑ ደጋፊ የሆኑ ምዕራባዊያን የሌሉ ተረኮችን መሰረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱና በማኅበራዊ ሚዲያ እንደሚነዱ ሲኤንኤን በቅርቡ የሰራውን ለአንድ ወገን ያደላ ዶክመንተሪ ፊልምን ማሳያ በማድረግ አቅርበውታል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በህወሓት ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ የተኩስ ማቆም ስምምነት ይደረስ በማለት በሌለ ነገር ላይ የሚያሳዩት ጣልቃ ገብነትም አቋማቸውን በግልጽ ያንጸባርቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረገና ለአንድ ወገን ያደላ ዜና እንዲሰራ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡

ቡድኑን በመደገፍ የውሸት ዜና በመፈብረክ የተጠመዱ ኃይሎች መሬት ላይ የሌሉ እውነታዎችን የሚጽፉ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ያለው ችግር የሚታወቅ ቢሆንም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚታየውን አለመረጋጋት 'ጆሮ ዳባ ልበስ' በማለት የትግራይን አጉልቶ ለማሳየት የሚያደርጉት ጥረት ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡

ርዝራዥ የህወሓት አባላት አሁንም በጥፋት መንገዱ የቀጠሉበት በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በማኅበራዊ ሚዲያ ጠላቶቹን ፊት ለፊት መጋፈጥ አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የሲ.ኤን.ኤን የተጭበረበረ ዶክመንተሪ በአክሱም ደረሰ የተባለውና ያልተደረገውን ጭፍጨፋ ለዓለም ለማሳመን የተፍጨረጨረውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተግባር መመከት የተባበረ ጥረት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም