በጃዊ ወረዳ -ፈንድቃ ከተማ በዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

150
ሀምሌ 24/2010 በአማራ ክልል በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ጃዊ ወረዳ -ፈንድቃ ከተማ በዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ  ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ  መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አስታወቁ። ኃላፊው እንደገለፁት በጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ይሰሩ በነበሩ ዜጎች ህይወት ላይ ትላንት ጉዳት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው  ተጀምሯል። በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ ግጭቶች በዜጎችና በንብረት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች አገር አቀፋዊና ክልላዊ ለውጡን የማደናቀፍ እንጂ ዳር የማድረስ ሚና አይኖራቸውም፤ ዜጎች ግጭትን ከሚያሰፍኑ ነገሮች በመቆጠብ ማንኛውንም ጉዳይ በውይይት ለመፍታት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል ሲሉ አቶ ንጉሱ በተለይ ለኢዜአ አመልክተዋል፡፡ የአካባቢው አመራርም ግጭቶች ወደ ሌላ መልክ ከማምራታቸው አስቀድሞ ከህብረተሰቡ ጋር በመምከር መፍትሄ ማበጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል። ትላንት በጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት ይሰሩ በነበሩ ዜጎች ህይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰማውን ሀዘን በመግለፅ ድርጊቱን ማውገዙና ጉዳዩን አጣርቶ አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ ወደ ስፍራው የአመራርና ባለሙያዎች ቡድን እንደላከ  መግለፁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም