የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት የአገራቱን ጥቅምና ፍላጎት ማክበር ላይ የተመሰረተ ነው - አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ

71

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 09/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሕንድ የአገራቱን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በማክበር የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን እያጎለበቱ እንደሚገኙ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ ገለጹ።

ሕንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የረጅም ዘመን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ጥረት እያደረገች እንደሆነም አምባሳደር ሮበርት ለኢዜአ ገልጸዋል።

አገራቸው በታሪኳ የኢትዮጵያ ፍላጎቶች ተቃዋሚ ሆና እንደማታውቅና ኢትዮጵያም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ለሕንድ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጋራ እንደሚሰሩና ሕንድ ማንኛውም አገር የራሱን ዕጣ ፈንታ በራሱ መወሰን አለበት የሚል መርህ እንዳላት ገልጸዋል።

ለአንድ አገር ሉዓላዊነት የሕልውና ጉዳይ ወሳኝ እንደሆነና ሉዓላዊነቱን በማስከበር የራሳቸው መዳረሻ መወሰን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የራሷን ጉዳዮች መፍታት ያለባት በራሷ ነው ያሉት አምባሳደሩ ሕንድ በዚህ መርኋ የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ ከማንኛውም አገር ጎን እንደምትቆም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያና ሕንድ ጠንካራ የፖለቲካ ትብብር እንዳላቸውና በቅርብ ጊዜ በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በየአገራቱ ያደረጓቸው ጉብኝቶች የዚሁ ማሳያ ናቸው ብለዋል አምባሳደር ሮበርት።

ሁለቱ አገራት በጋራ መግባባትና መከባበር እንዲሁም በእውነተኛ ትብብር ላይ የተመረኮዘ ጠንካራ የልማት ትብብር አላቸው ነው ያሉት፤ የልማት ትስስሩ የደቡብ ደቡብ ትብብር ማሳያ መሆኑንም አመልክተዋል።

በልማት ትብብሩ ሕንድ ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሰጠቻቸው ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍና በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድርና የቴክኒክ ስልጠናዎች በመስጠት የአቅም ማጎልበት ስራ እየሰራች እንደሆነ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያና ሕንድ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.አ.አ በ1948 ነው።

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱና ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከ584 በላይ ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን ግብርና፣ የአበባ ምርት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ምህንድስናና መድሐኒት ኩባንያዎቹ ከተሰማሩባቸው መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ የከበሩ ድንጋዮች፣ የተለያዩ የእህል ዘሮችና ጥራጥሬዎች፣ አትክልትና ቆዳ ወደ ሕንድ ስትልክ የብረታብረት ውጤቶች፣ ማሽኖችና መሳሪያዎች እንዲሁም መድሐኒቶችን ታስገባለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም