ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ለመፍታት የሚያግዝ የስልጠና ማዕከል አቋቋመ

63

ጅማ፤ ሚያዚያ 09/2013(ኢዜአ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር በሳይንስና ቴክሎጂ ለመፍታት የሚያግዝ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ የሚያዳብር የስልጠና ማዕከል ማቋቋሙን ገለጸ።

በማዕከሉ እንቅስቃሴ ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን ውይይት በተደረገበት ወቅት እንደተመለከተው፤ ማዕከሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ከማሳደግ አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በውይይት መድረኩ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ እንዳሉት፤ ተቋሙ "ስተም ፖውር " ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን ማዕከሉን ማቋቋማቸው ተማሪዎች በሳይንሱ ዘርፍ ውጤት ለማምጣት ያግዛቸዋል፡፡

በተለይ በማህበራዊ ኑሮ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚፈቱ ፈጠራዎችን ዩኒቨርሲቲው እንደሚያበረታታ ገልጸው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገት የሚያበቁ ሁለት ቤተ ሙከራዎችና ኮምፒተሮች ለማዕከሉ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በቅርቡም በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሂሳብ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች በመቀበል ስልጠና መስጠት እንደሚጀምሩም አሰታውቀዋል፡፡

ይህም በተለይ የማህበረሰቡን ችግር በሳይንስና ቴክሎጂ ለመፍታት እንደሚረዳ ተመልክቷል።

የ"ስተም ፓወር " ድርጅት ሀላፊ ወይዘሪት ቅድስት ገብረአምላክ በበኩላቸው፤  ድርጅቱ ተማሪዎች በፈጠራ እንዲበረታቱ፣ ሳይንሳዊ ትምህርት እንዲዘምን ፣ የመፍጠር ፍላጎትና አቅምን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን በሳይንሳዊ ዘዴ መፍታት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ሀገርን የሚጠቅሙ ስራዎች  እያካሄዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በአሜሪካ እንደተመሰረተ ጠቅሰው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ53 የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ተመሳሳይ ማዕከላት ማቋቋማቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም