ከ600 ሺህ በላይ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሃብታቸውን አስመዝግበዋል

84

አዲስ አበባ ሚያዚያ 09/2013 (ኢዜአ) የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከ600 ሺህ በላይ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሃብትና ንብረታቸው ማስመዝገባቸውን አስታወቀ።

በመድረኩ በከተሞች የሚከናወኑ ተቋማዊ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች፣ የሚስተዋሉ የሙስና እና ብልሹ አሰራር ቅሬታና አቤቱታ አቀራረብ እና የሃብት ማስመዝገብ ሥራዎች የዘጠኝ ወር ሥራ አፈጻጸምን በአዳማ ገምግሟል።

በውይይት መድረኩ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደሮችና ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።

በከተሞች መሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራር ቅሬታን ለመፍታት ከዕቅድ ዝግጅት እስከ ትግበራ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውና በ52 ከተሞች የድጋፍና ክትትል ሥራ መሰራቱ ተገልጿል።

የፌዴራል የስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሃብት ምዝገባ ተከናውኗል።

በፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በልማት ድርጅቶች፣ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በተሻለ መልኩ ሃብት አስመዝግበዋል ብለዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ በዕቅድ ከያዘው 95 በመቶውን ማሳካት እንደቻለ ነው ያስረዱት።

በክልሎችም ከአፋርና ሶማሌ በስተቀር ሲዳማ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሐረሪ እና ኦሮሚያ በሀብት ማስመዝገብ የተሻለ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችና በሌሎች የፌዴራል ተቋማት ከ600 ሺህ በላይ ሠራተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ሃብታቸውን አስመዝግበዋል።

በኮሚሽኑ የከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሪት ማክዳ ጌታሁን በበኩላቸው በ117 ከተሞች የተለያዩ የመሰረተ ልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ሂደቱ ከሙስናና ብልሹ አሰራር የጸዳ መሆኑን ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ ከየከተሞች በሚላኩ ሪፖርቶች መሰረት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን እንደሚለይና ለዓለም ባንክ በዓመት ሁለት ጊዜ ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ ለከተሞች ተቋማዊ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ በአምስት ዓመታት የሚተገበር ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድቦ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

የፌዴራል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አዋጅ ቁጥር 1136/2013 ማንኛውም የመንግስት የሥራ ኃላፊና ሠራተኛ ሃብትና ንብረቱን ማስመዝገብ እንዳለበት ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም