የአገሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በጥናትና ምርምር ለመመለስ እየተሰራ ነው - የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

78

አዲስ አበባ መጋቢት 09/2013 (ኢዜአ) በአገሪቷ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በጥናትና ምርምር ለመመለስ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የምርምር፣ የሣይንስና የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎችን የስራ ዕቅድና አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ እያካሔደ ነው።


የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሣሙኤል ኡርቃቶን ጨምሮ የምርምር፣ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንቶች በመድረኩ እየተሳተፉ ነው።


በግምገማ መድረኩ ሚኒስቴሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ገበያውን ባማከለ መልኩ በተልዕኮ የመለየት ስራውን ማጠናቀቁ ተገልጿል።


ይህ ተቋማትን በተልዕኮ የመለየት ተግባር ተቋማቱ ተወዳዳሪና ብቃት ያላቸው ምሩቃንን እንዲያፈሩ ያስችላል ተብሏል።


በመጪዎቹ 5 ዓመታትም በአገር በቀል የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች 5 ሺህ የዶክትሬት ምሩቃንን ለማፍራት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።


ሚኒስቴሩም ተቋማት ያላቸውን ግብዓትና የሰው ሃይል በማስተባበርና በማቀናጀት የተደራጀ አቅም ለመፍጠር  እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።


የአገሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በጥናትና ምርምር ለመመለስ እንዲቻል የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ተለይተው የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ተመልክቷል።


ዩኒቨርሲቲዎቹ በዋናነት አሻጋሪና ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማካሔድ የአገሪቷን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው በመድረኩ የተነሳው።


ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ይገመገማል፣ የቀጣይ ስድስት ወራት ዕቅድ ላይም ውይይት ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል።


አዲስ አበባ፣ ሃዋሳ፣ ሃሮማያ፣ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ አርባምንጭ፣ ጅማ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ዩኒቨርሲቲ ተብለው መለየታቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም