አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ ነው - ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል

73

ሚያዚያ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) በተለያዩ ጉዳዮች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ የተጀመሩ ስራዎች ውጤት እያስገኙ መሆኑን የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የሠላም ሚኒስትሯ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተቋማቸው ባለፉት ሶስት ዓመታት በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

"ለዘመናት የተከማቸ ችግርን በአንድ ጀንበር መፍታት አይቻልም" ያሉት ሚኒስትሯ፤ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በሰለጠነ መንገድ በውይይት የመፍታት ልምድ ማዳበር አንደኛው መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ በሚኒስቴሩ የሚዘጋጁ ስልጡን የውይይት መድረኮች ውጤት እያስገኙ መሆኑን ነው የገለጹት።

በእነዚህ የምክክር መድረኮች ምሁራንን ጨምሮ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችና በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ናቸው።

ሚኒስትሯ በውጤታማነቱ ስምንት የሙያና የብዙሃን ማኅበራት የሚሳተፉበትና የሚያስተባብሩትን የውይይት መድረክ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በሌላ መልኩ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በውጭ የሚኖሩ የታጠቁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሠላማዊ መንገድ እንዲወዳደሩ የማሳመኑ ስራ ሌላው ውጤት መሆኑን አንስተዋል።

መሰል ውይይቶች አለመግባባቶችን በሠላማዊ መንገድ ከመፍታት ባለፈ ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ለዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት የተናገሩት።

የሠላም ግንባታ ስራ አድካሚና አሰልቺ የመሆኑን ያህል በአንድ ጊዜ ውጤቱን ማየት ከባድ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቸው የሚያከናውናቸውን የዘላቂ ሠላም ግንባታ ስራዎች ሁሉም ዜጋ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

ሚኒስቴሩ እየገነባ ያለው የቅድመ ማስጠንቀቂያና የፈጣን ምላሽ ስርዓት በየአካባቢው የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም